አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች ሃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

52
ጥቅምት 11 / 2012 ዓም ጅግጅጋ ኢዜአ በሶማሊ ክልል በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የክትባት ሽፋን ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላትና የጤና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸው በአግባቡ እንዲወጡ የክልሉ መንግሥት አሳሰበ። የክልሉ ጤና ቢሮ በበኩሉ ለወረዳ ጤና ጽህፈት ቤቶችና ለጤና ተቋማት ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎችን በሁሉም ዞኖች አሰማርቻለሁ ብሏል ። የክልሉ ርእሰ መስተዳደር  ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ ዩሱፍ የክትባት ሽፋን ለማሳደግ ለባለድርሻ አካላት በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት  በክልሉ ባለፉት ዓመታት በጤና ተቋማት ግንባታና በሰው ሀይል ስልጠና የተሻለ ውጤት ተመዝገቧል። ሆኖም ግን "በገጠር አካባቢ የሚመደቡ የጤና ባለሙያዎች በስራ ቦታ አለመገኘትና የአመራር ክትትል ማነስ ምክንያት ህብረተሰቡ ክትባትን ጨምሮ ተገቢውን የጤና አገልግሎት አያገኝም" ብለዋል ። ለአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ የተሻለ የጤና አገልግሎትን ለማዳረስና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለውን የህፃናት ክትባት ሽፋን ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላትና የጤና ባለሙያዎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዩሱፍ መሐመድ በበኩላቸው በክልሉ መደበኛ ሙሉ የክትባት ሽፋን የሚያገኙ ህፃናት አስራ አንድ በመቶ ብቻ መሆኑን  ገልጸዋል ። "ክልላችን በክትባት በኩል ከሌሎች ክልሎች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው " ያሉት ኃላፊው ጤና ቢሮው ከክልሉ መንግስትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አገልግሎቱን ለማሻሻል በቁርጠኝነት አየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ። የክትባት አገልግሎት ሽፋኑን አናሳ የሆነበት ምክንያት በመለየት ለጤና ተቋማት በቅርበት ድጋፍ መስጠት እንዲቻል  ባለሙያዎች በሁሉም ስፍራ እንዲሰማሩ መደረጉን ከዶክተር ዩሱፍ መሀመድ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።
     
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም