ወቅታዊ ተግዳሮችን ለመፍታት ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተገለፀ

191
ጥቅምት 11 / 2012... በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ወቅታዊ ተግዳሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ማህበረሰቡ ለዘመናት ያዳበረውን የባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ መከተል እንዳለበት በዘርፉ ጥናት ያካሔዱ ምሁራን ተናገሩ ። የወሎ ዩኒቨርሲቲ “የኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀት ዳሰሳ ለሰላምና ልማት እድገት” በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት ባካሄደው 5ኛው አገር አቀፍ የባህልና ኪነ ጥበብ አውደ ጥናት ላይ ዘርፉን የሚመለከቱ 15 ጥናቶች ቀርበዋል። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ-ጹህፍ መምህርና የግጭት አፈታት ተመራማሪ ዶክተር ገብረየሱስ ተክሉ  እንዳሉት ኢትዮጵያ ለሌሎች አገሮች የሚተርፍ ታሪክ፣ ባህልና እሴቶች ያላት አገር መሆኗን ዓለም የመሰከረው ሃቅ ነው ብለዋል ። "ለአንድነትና ሰላም አክራሪ ብሄርተኝነት ወይስ ባህላዊ እሴት ማጎልበት"  በሚል ርዕስ በቀረቡት ጥናት ላይ እንደገለፁት ምንም እንኳን አገራችን የታሪክና የባህል ጸጋዎች ባለቤት ብትሆንም በአሁኑ ጊዜ በአጉል መጤ ባህል እየተበረዘ እንደሚገኝ አስረድተዋል ። አባቶቻችን ለዘመናት ያደበሩትን ጥንታዊው የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶች እየተረሱ በመምጣታቸው ቋንቋ፣ ባህልና ሌሎች ጸጋዎች የአገር ኩራት መሆናቸው ቀርቶ የልዩነትና ያለመግባባት መፈጠር ምክንያት ሲሆኑ ማየት የተለመደ ሆኗል። በተለይም በሁለንተናዊ ተዛምዷቸው ከፍተኛ በሆኑት በትግራይና አማራ ክልሎች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በአባቶች ሽምግልናና በሀይማኖት አባቶች ውይይት ከመፍታት ይልቅ በመግለጫ ጋጋታ፣ በፉከራ፣ በዛቻና በእልህ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተገቢነት የለውም ብለዋል። ህብረተሰቡ ላይለያይ በደም የተጋመደና የተዋለደ በመሆኑ መለያየትን ሳይሆን አንድነትንና አብሮነትን አብዝቶ የሚናፍቅ እንጂ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ለጦርነት የሚዘጋጅ ስነ ልቦናና ፍላጎት እንደሌለው በዳሰሳ ጥናታቸው እንዳረጋገጡ ገልፀዋል ። በመሆኑም በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች እኔ የበላይ አንተ የበታች በሚል የተሳሳተ ትርክት በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሳውን የጸጥታ ችግር በባህላዊ ግጭት አፈታት ዘዴ በመፍታት የድሮውን ሰላምና አንድነት መመለስ እንደሚቻል በጥናታዊ ፅሁፋቸው አለመላክተዋል። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጅ መምህርና የሰላምና ልማት ተመራማሪ አቶ ጉባይ አሳዬ "ጥቁር ደም" በሚል ርዕስ በቀረቡት ጥናት በአንዳንድ አካባቢዎች በበቀል ደም እንመልሳለን እየተባለ በፉክክር የሚቀጥለው የመገዳደል ስሜት ኋላቀርነትን የሚያመላክት ነው ብለዋል ። ወንጀል የፈጸመውን ግለሰብ በህግ ቀርቦ እንዲቀጣ ከማድረግ ይልቅ በቂም በቀል የሚካሄድ መገዳደልን ለማስቀረት በአገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች የሚካሄደው እርቅ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መሰረት በመሆኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል ። አስታራቁዎቹ የተለያዩ ዘዴዎችንና እምነቶችን ተጠቅመው ግድያው እንዳይደገም፣ ቂም እንዳይኖርና አብረው ሰርተው እንዲበሉ ለማስቻል የግጭቱን መንስኤ በመለየት የተመጣጠነ ካሳ እንዲከፈል ስለሚያደርጉ እርቁ የጸና ይሆናል ብለዋል። በኢትዮጵያ ያሉ አቀር በቀል እውቀቶችን በጥናት በመለየትና በማጎልበት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት የአገር በቀል እውቀቶች ጥናትና ምርምር ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልፈታ አብደላ ናቸው፡፡ ከ130 በላይ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች ቢኖሩም በግንዛቤ እጥረትና በቸልተኝነት ስራ ላይ እንዲውሉ ባለማድረጉ አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ አለመጋባባቶችን በዘላቂነት መፍታት ክፍተት መፈጠሩን ተናግረዋል ። ከላይ ከተጠቀሱት ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች ወስጥም 10ሩን በማጥናት በመጽሐፍ መልክ ታትመው የወጡ ሲሆን 45 የሚሆኑት ደግሞ በመጠናት ላይ መሆናቸው አመልክተዋል። በሰላም ሚኒስተር የሰላም እሴቶች ግንባታ ባለሙያ አቶ ትዕዛዙ ደለለው በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው በጥናት የተደገፉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ተጠቅሞ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎችና ከሐይማኖት አባቶች ጋር በቅንጅት በዘላቂነት ለመስራት የሚያስችል በበጀት የተደገፈ የህግ ማቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር  ሽማግሌዎች፣ የዩኒቭርሲቲ ሙህራንና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተሳትፈዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም