በዋግህምራ ብሄረሰብ የእለት ደራሽ እርዳታ እየተሰጠ ነው

74
አዲስ አበባ  ጥቅምት 11/2012 በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ 126 ሺህ ሰዎች የእርዳታ እህል እየተከፋፈለ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ እታገኘሁ አደመ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በአማራ ክልል ዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በዘንድሮው ድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ 126 ሺህ ሰዎች ለአንድ ወር ቀለብ የሚሆን 18 ሺህ 900 ኩንታል እህል እየተከፋፈለ ነው ። የድርቅ ተጎጂዎቹ ለመደገፍም ከኮሚሽኑ በተጨማሪ የውሃ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት የተካተቱበት አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልፀዋል። ፈጣን ዳሰሳ በማካሄድም ለጊዜው የተለዩ ሰዎች በፍጥነት ምግብ እንዲደርስ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እህል ማከፋፈል መጀመሩን አስታውቀዋል። እስከ አሁንም በደሃና ወረዳ አምደ ወርቅ አካባቢ ለ15 ሺህ ሰዎች የምግብ እህሉ መከፋፈል መጀመሩን አመልክትው በዚህ ሳምንት ሙሉ በሙሉ የማጓጓዝና የማከፋፈል ስራው እንደሚጠናቀቅ አብራርተዋል። ከምግብ እህሉ በተጨማሪ ዘይትና ክክ እየቀረበ መሆኑን አመልክተው ለእነዚህ ሰዎች የሚደረገው ድጋፍ ዓመቱን ሙሉ የሚቀጥል እንደሆነም ጠቅሰዋል። ድርቁ ያስከተለውን የምግብ ክፍተትም መንግስት የመሸፈን ሙሉ አቅም እንዳለው የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሯ ከመንግስት እውቅና ውጭ በማንኛውም መንገድ የሚከናወን የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባር ተቀባይነት የለውም ብለዋል። የመደገፍ ፍላጎቱም ሆነ አቅሙ ያለው ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ከመንግስት ጋር በመተባባር በመንግስት የአሰራር ስልት ውስጥ ተካትቶ መከናወን እንዳለበትም አስታውቀዋል። ችግሩ በሳህላና ዝቋላ ወረዳዎች የሚኖሩ ሰዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለእርዳታ መጋለጣቸውን አመልክተው በሌሎች አካባቢዎች ከፊል ድጋፋ እንደሚደረግ አመልክተዋል። በክልሉ በቀጣይም ከዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በተጨማሪ በሌሎች ተመሳሳይ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን ለመለየት እየተሰራ እንደሆነም ታውቋል። በተለይም በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦና ሃብሩ ወረዳዎች፣ በማዕከላዊ ጎንደር ምስራቅ በለሳ፣ በሰሜን ጎንደር ጃናሞራ ወረዳዎች ተመሳሳይ የድርቅ ችግር በመከሰቱ በቀጣይ በጥናት የመለየት ስራ ይከናወናል። በሚቀርበው የልየታ ጥናት መሰረትም ከመጭው ጥር ወር ጀምሮ የምግብ እህል እንዲቀርብላቸው እንደሚደረግ አብራርተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም