የሩሲያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የመሰረተልማት ፕሮጀክቶች ለመሳተፍ ፍላጎት አለው... አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን

78

ኢዜአ፤ ጥቅምት 11/2012 በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን  ከታስ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።

ለኢትዮጵያ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ጥራት ያለው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸው፥ ለዚህም የባቡር መሰረተ ልማት ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር አያይዘው የሩሲያ መንግሥት የምድር ባቡር ኮፖሬሽን በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ  የኒዩክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል  ከሩሲያው  የሮሳቶም ኮርፖሬሽን ጋር ለመስራት መታሰቡን እና ሶቺ ላይ የስምምነት ፊርማ እንደሚኖርም ተናግረዋል።

ኒዩክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ጥቅም የማዋል ስምምነት ተፈርሞ ወደ ስራ ከገባ በኋላም በግብርና፣ በህክምና፣ በኃይል ዘርፍ በትብብር እንደሚሰራም ነው ያነሱት።

የኒዩክሌር የምርምር ማዕከል በኢትዮጵያ እንደሚከፈትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርታማነት አሁንም አነስተኛ መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ኢቭጌኒ፤የተወሰኑ የሩሲያ የግል ኩባንያዎች የግብርና መሳሪያዎችን፣ ማዳበሪያ ለማቅረብ እና የቴክኖሎጂ እውቀት ልምድን ለማካፈል ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም