ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የምትሰጠው በውጭ እንጂ በውስጥ ጉዳይዋ አይደለም - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

65
አዲስ አበባ፤ ኢዜአ፤ ጥቅምት 11/2012 ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የምትሰጠው በውጭ ጉዳይ እንጂ በውስጥ ጉዳይዋ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ እንዳሉት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን የምታጠናክረው የባህር በር የሌላት እንደመሆኗ ለራሷ ሠላምና ጥቅም ስትል ነው። እንደ እርሳቸው ገለጻ በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደተመለከተው የውጭ ግንኙነቷን ለማጠናከር አበክራ ትሰራለች። ነገር ግን ከውጭ አገራት ጋር ያለው ግንኙነት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሳይሆን ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል። 'ለምሳሌ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ጎረቤቷ ብቻ ሳትሆን ከሌሎች ወዳጅ አገራት ጋር የምታገናኘን የመውጫ በራችን ናት' ብለዋል። ለእነሱ 'ትኩረት እንሰጣለን' የሚለው መነሻ ሃሳቡ የአገር ውስጥ ፍላጎት እንደሆነ በመጠቆም። ሱዳንም ለኢትዮጵያ ጎረቤት ብቻ ሳትሆን አንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን የሚኖሩባት በመሆኗ 'የሱዳን ሠላም የእኛ ዜጎች ጉዳይ መሆኑን ማሰብ አለብን፤ ጅቡቲም ውስጥ እንዲሁ' ሲሉ ተናግረዋል። 'ለጎረቤት ቅድሚያ እንሰጣለን ስልን ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከሌሎች የዓለም አገራት መሆኑ ሊታሰብ ይገባል' ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ከጎረቤት አገራት ጋር ያለው ግንኙነት በዘር በሃይማኖት በቋንቋና በብዙ ምክንያት የተሳሰረ በመሆኑ የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል። በጋራ የምናድገው "ከአገራቱ ጋር ያለንን ሰጥተን የሌለንን ተቀብለን ስንሰራ ነው" ያሉት ዶክተር አብይ "በውጭ ግንኙነታችን ከአሜሪካና ከቻይና በፊት ጎረቤት አገሮቻችንን እያስቀደምን እንቀጥላለን" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም