መንግስት ለአገር ውስጥ ሰላም ትኩረት ሰጥቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

76
አዲስ አበባ፤ኢዜአ፤ ጥቅምት 11/2012 የኢትዮጵያ መንግሥት ለአገር ውስጥ ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት በተለያዩ አካላት መካከል የቆዩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ረግበው በአገሪቱ የውስጥ ሰላም እንዲረጋገጥ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል። ከሰላም ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክልሎችም በመጓዝ ጭምር በሰላም ዙሪያ ከየአከባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ተደርጓል ሲሉም ገልፀዋል። በኦርቶዶክስ ቤተ ክረስቲያንና በሙስሊሙ ማህበረሰብ መካከል የነበረውን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት የተደረገውን ጥረት አንስተዋል። የእምነት ተቋማቱን ወደ አንድ ማምጣት ለአገር ሰላም ቅድሚያ አለመስጠት ነው ብሎ የሚያምን ግለሰብ ካለ ስህተት ነው ብለዋል። መንግሥት የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን እንደ አንድ ጠንካራ ተቋም እንደሚመለከትና ለአገር ሰላምና ብልጽግና ትልቅ አብርክቶም እንዳለው ያምናል ነው ያሉት። አክለውም "ያለፈው ረማዳን ሙስሊሞች አንድ ሆነው ባይሆን ኖሮ ምን አልባት ብዙ ነገር አሁን እንደምናየው ላይሆን  ይችል ነበር፤ አቅለን ማየት የለብንም" ብለዋል። የሰላም ሚኒስቴርና የእርቅ ኮሚሽን መቋቋማቸው መንግስት ለውስጥ ሰላም መረጋገጥ እየሰጠ ያለውን ቅድሚያ ትኩረት መሰጠ ያረጋግጣልም ብለዋል። በኢትዮጵያ ያለው ሰላም ግጭትን የማስቆምና አንጻራዊ ሰላም የማግኘት ሁኔታ እንጂ ዘላቂና ነጻነትን እስከማጎነጸፍ የሚደርስ አዎንታዊ ሰላም ኖሮ አያውቀም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንዲያም ሆኖ በተለያዩ አካባቢዎች ሚቀሰቀሱ ግጭቶችን ለማረጋጋት መስዋዕትነት ለሚከፍሉ የሰራዊት አባላት ምስጋና አቅርበዋል። ይህንን አዎንታዊ ሰላም እውን ለማድረግ ደግሞ ሀሉም የአገሪቱ ሕዝቦች ከራሳቸው ከቤተሰባቸው ጀምሮ ሰላምን ለማረጋገጥ መስራት አለባቸው ነው ያሉት። ዜጎችን ማፈናቀል ንግድ የሆነበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው የተፈናቀሉትን ሰዎች ቁጥር በመጨመር ያልተገባ ገቢ ለመሰብሰብ የሚሰሩ አካላት መኖራቸውንም ተናግረው፤ ለአብነትም ከጌዲዮ ዞን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተፋናቅሏል ተብሎ የተወራው በተግባር ከ200ሺ በላይ እንደማይበልጥ ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል። ያም ሆኖ በመፈናቀል ደግሞ የተቸገሩ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸው እነርሱንም ወደ ቀያቸው የመመለስ ተግባር መከናወኑን ነው ያብራሩት። ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከውጭ ወደ አገራቸው ኢንዲመለሱ መደረጉ  የአገር ሰላምን ለማስጠበቅ ከሚል እሳቤ የተነሳ መሆኑን አስረድተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የአገር ውስጥ ሁለንተናዊ ሰላም የሚረጋገጠው በቅርብ ጎረቤት አገራት ያለው ሰላም የተረጋገጠ ሲሆን መሆኑን በመገንዘብ መንግስት ለአካባቢው አገራት ሰላም እየሰራ እንደሆነ አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ከማንም በላይ ቅድሚያ ትኩረት የምትሰጠው ጅቡቲን፣ ሱዳንን፣ ኤርትራንና የመሳሰሉ የጎረቤት አገራት መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ኢትዮጵያን ጨምሮ ጎረቤት አገራት በምጣኔ ኃብት ብቻ ሳይሆን በዘር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት የተሳሰሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል። በእነዚህ አገራት ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ዓይነት ችግር በኢትዮጵያ ላይ የጎላ ተፅእኖ የሚያስከትል በመሆኑ ለአገራቱ ሰላም ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያ ያለጎረቤት አገራቱ፤ የጎረቤት አገራቱም ያለኢትዮጵያ መኖር እንደማይችሉ በመጠቆም።                                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም