የክልሎች ግንኙነት በመደጋገፍ ላይ የሚመሰረት እንጂ በጠላትነት መፈላለግ መሆን የለበትም

112
ጥቅምት 11 /2012 በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት በመደጋገፍ ላይ የሚመሰረት እንጂ በጠላትነት መፈላለግ መሆን የለበትም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ ጉባዔ ላይ ተገኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የምክር ቤቱ አባላት በክልሎች መካከል የሚታየውን የትጥቅና የፉክክር ጉዳይ አንስተው ምላሽ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያም በኢትዮጵያ ትልቁ ችግር 'ካለፈው ስህተት አለመማራችን ነው' ብለዋል። ለዚህም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከ13-15 ሚሊዮን ሕዝብ መሞቱን፤ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ትምህርት ባለመወሰዱም ከ65 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን አንስተዋል። በኢትዮጵያም 'ባለፉት 40 ዓመታት በእርስ በእርስ ግጭት በርካታ ቁጥር ያለው ዜጋ አልፏል' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እግራቸውን፣ እጃቸውን ዓይናቸውን አጥተው ለወላጆቻቸው ሸክም የሆኑ መኖራቸውን መገንዘብ ይገባል፤ ከትናንትናው ኪሳራ መማር ያስፈልጋል ነው ያሉት። ''በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ፓርቲዎች መፍትሄ የሚገኘው በመሳሪያና በጦርነት ነው ብለው የሚያምኑ ዛሬም አሉ'' ያሉት ዶክተር አብይ እነሱ ወጣት ማስገደል እንጂ መሞት አያውቁም የኢትዮጵያ ሕዝብ መንቃት አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል። ወጣቱ በአገሪቷ የተለያዩ ቦታዎች ግጭት እየቀሰቀሱ መኖርና ማትረፍ የሚፈጉ መኖራቸውን በመገንዘብ መንቃት አለበት፤ መሰል አስተሳሰብ ከዘመኑ ጋር አይሄድምና 'በቃችሁ' ሊላቸው ይገባል ብለዋል። በክልሎች መካከል ስላለው ግንኙነት ሲያብራሩም የትግራይን ክልል የሚያስተዳድረው መንግሥት ቀን ከሌሊት ስለ ውጊያ ነው የሚያስበው ብለው የሚያምኑ መኖራቸውን ጠቁመዋል። ሆኖም ክልሉን እየመሩ ያሉት ጥቂት አመራሮች የትግራይን የውኃና የልማት ችግር መፍታት እንጂ ከአማራ ወይም ከሌላ ክልል ጋር ወደ ግጭት የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረዋል። የአማራ፣ የትግራይም ይሁን የኦሮሚያ ሕዝብ 'ወደ ግጭት የመግባት ፍላጎት የለውም' ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ከትጥቅ ጋር በተያያዘም ክልሎች መዘጋጀት ያለባቸው የራሳቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ እንጂ ከሌላ ክልል ራሳቸውን ለመከላከል መዘጋጀት የለባቸውም፤ ቢፈልጉም አይችሉም ወደ ማያባራ ጦርነት ይገባሉ እንጂ በዘላቂነት አሸናፊ መሆን አይቻልም ሲሉ አብራርተዋል። ''አንዱ ክልል ለአንዱ መከታ ነው መሆን ያለበት ይህ ከሆነ ልማትና መሻገር ይመጣል፤ አሁን ባለው የፖለቲካ ትኩሳት ሕዝቡ ውኃ ጠማኝ እያለ ድህነትን ሳናሸንፍ ሁለተኛ ደረጃ እንኳን 50 በመቶ ሳይኖረን ክላሽ ብዙ አይጠቅመንም ሕዝቡም እየነቃ ይሄዳል የሚል እምነት አለን'' ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የፌዴራል መንግሥት የማስተካከያ እርምጃዎች ይወስዳል ሲሉም ተደምጠዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም