"ዓይንና ጆሮ ለጣና"

105
ከእንግዳው ከፍያለው ከኢዜአ ጧት 12 ሰዓት ከባህርዳር ከተማ ተነስተን ጉዟችን ወደ ምስራቅ አቅጣጫ አድርግናል። ዕድሜ ጠገቡ የአባይ ድልድይ ላይ ስንደርስ የወንዙን ፍሰት በመኪናው መሰኮት ተጠግቼ አየሁት። ከወትሮው በተለየ መልኩ ፍሰቱ ጨምሮ ወንዙ ከአፍ እስከ ደገፉ ሞልቶ መፍሰሱን ቀጥሏል። ምንም እንኳ ወቅቱ ጥቅምት ቢሆንም የአባይ ወንዝ አሁንም አፈር ይዞ መጓዙን አለመቀነሱን የውሃው አለመጥራት ያሳብቃል። ሰኔና ሃምሌ ወር ላይ የጨረጨራ ግድብ በመዘጋቱ ምክንያት የአባይ ወንዝ ፍሰት በመቀነሱ በውስጡ ያሉ ድንጋዮች እንኳን ፍጥጥ ብለው እየታዩ ነው የከረሙት። እንዳውም የወንዙን ፍሰት በአንድ አቅጣጫ ለማድረግ ሁለት እስካቬተር ገብተው ሲያጸዱ የነበሩት ሃምሌ ወር ላይ ነው። ሰኔ እና ሃምሌ ወር ላይ ግድቡን በመዝጋት ደለሉ ጣና ላይ እንዲከማች በማድረግ ውሃው በሚጠራበትና ከደለል ነጻ በሚሆንበት አሁን ላይ  ውሃውን መልቀቅ ምን ይሉታል ? ። የኛን አገር አመራርና ባለሙያ ትዝብት የጣለውም መስራት ያለበትን ነገር መቼ፣ እንዴትና ለምን እንደሚሰራው አውቆ በመርህ አለመተግበሩ ነው ። ጣናን ሰኔና ሃምሌ ገድቦ ዛሬ መለቀቁም የዚሁ ችግር ማሳያ ነው ብዬ እያሰብኩ ጉዞየን ቀጥያለሁ። ምንም እንኳ ገና ጧት ላይ ወረታ ብንደርስም ወንድ ልጅ መዋያውን አያውቅምና ቁርስ እንብላ ብለን አርፈናል። ቁርሳችን በልተንና ቡና ጠጥተን ጉዞ ወደ ጎንደር ቀጥለናል። አዲስ ዘመንን አልፈን የድንጋይ ምሰሶ ከተራራው ጥግ ከሚታይበት አካባቢ ስንደርስ የመኪናችን ጎማ በመተንፈሱ ሹፌሩ አቁሞ ጎማ መቀየሩን ተያይዞታል። እኛም በአረንጓዴ የተሸፈነና ተራራማ በመሆኑ ተማርከን አካባቢውን ፎቶ ማንሳት እያነሳን ቆየን ። ጎማውን ቀይሮ ሲጨርስ ተሳፈርንና ጉዞ ወደ ጎንደሯ ማክሰኝት ቀጠልን። ከማክሰኝት ሳንደርስ አንዲት ትንሽ ከተማ ላይ የተበላሸውን ጎማ ሹፌሩ ሊያሰራ መኪናውን አቆመ። ሰሞኑን በጎንደር አካባቢ ሁከትና ብጥብጥ እንዳለ በሚዲያ ሲዘገብ ስለነበር የት አካባቢ እንደሆነ አንዳችንም የምናውቀው ነገር የለም። ሹፌሩም ጎማውን አሰርቶ ጉዟችን ቀጠልን። ማክሰኝት ልንደርስ ሁለት ኪሎ ሜትር ሲቀረን መኪናው አስፓልቱን ለቆ ወደ ደቡብ አቅጣጫ አመራ። ጠጠር መንገድ በመሆኑ ተጠንቅቆ መጓዝ ይበጃል አልኩ በልቤ። ካልሆነ መኪናው ሲነጥር ከመኪናው ኮፈን ጋር ነጥሮ መጋጨት እንዳለ ከአንድ ሁለት ጊዜ አጋጥሞኛል። ከዛ በኋላ ዳር ስለነበርኩ በአንድ እጄ ከፊት ለፊቴ ያለውን ወንበር በመያዝ አደጋ እንዳይደርስብኝ እራሴን ጠብቄ እየተጓዝኩ ነው። ሌላውም እንዲሁ። ትንሿን ኮረብታ አልፈን ብቅ ስንል ለብዙ ዓመት ከእንስሳት ንክኪ ተከልክሎ የተከበረ መስክ የመሰለ አረንጓዴ የለበሰ ወለል ያለ ሜዳ መስሎ ታየን። ሹፌራችን ይሄ የምታዩት የጣና ሀይቅን የሸፈነው እምቦጭ ነው አረንጓዴ መስሎ የሚታየው አለን። ሃይቁን ለማየት አይኔ ቢያማትር ማየት እስከሚችለው ጥግ ድረስ በእምቦጭ የተሸፈነ አረንጓዴ ሜዳ እንጂ የውሃ ክፍል አልታይ ብሎኛል። እየተጠጋን ስንመጣ አሁን ወቅቱ እምቦጭ የሚያብብበት ወቅት በመሆኑ አልፎ አልፎ በነጭ፣ በሰማያዊ፣ ቀይና በሌሎች ቀለማት ፈክቶ ይታያል። የቀለማት ውህዱ ህብር ፈጥሯል። ማማርና ውበት የድምቀት መሆኑ ቀርቶ የጥፋት ከሆነ ምን ያደርጋል አልኩ በልቤ። እምቦጭም በአረንጓዴ ልምላሜውና በህብር ፍካቱ ቢያምርም የጣና ሃይቅን ለማድረቅ የተላከ እርኩስ መንፈስ ሆኖ ታየኝ። ሃሳቡ የኔ ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው አርሶአደሮችም እውነት መሆኑን በቃለ መጥይቄ አረጋግጫለሁ። ዓይን ያለው ሰው የጣና ሃይቅ በአገራችን ትልቁ ሃይቅ መሆኑን አይቶ መገመት አያቅተውም። ያላየም ቢሆን ስለ ጣና ሃይቅ ታላቅነት ሳይሰማ አይቀርም። የጣና ሃይቅ ትልቅ ብቻ ሳይሆን 60 በመቶ የሚሆነው የአባይ ውሃ የሚመነጨውም ከዚሁ ሃይቅ መሆኑን ተመራማሪዎች የጻፉትን ሳያነብ የሚቀር ያለ አይመስለኝም። ካላነበበም ሲተረክ፣ ሲነገር፣ ሲወራና ሲዘመር ሳይሰማ አይቀርም ። 28 ዓይነት የአሳ ዝርያዎች በሃይቁ ውስጥ መኖራቸውን መቼም በባህርዳር፣ በጎርጎራ፣ በጎንደርና ሌሎች የአቅራቢያ ከተሞች በሚገኙ የዓሳ ዱለት፣ጥብስ፣ ኮተሌት… የተመገበ ሰው መገንዘቡ አይቀርም። ወይም ከአካባቢው ሰዎች፣ ከምሁራንና ሌሎች ሙያተኞች ጋር ሲያወሩ ሆነ በሹክሹክታ ሳይሰማ የሚቀር ያለ አይመስለኝም። ከዓሳ ዝርያዎቹ ውስጥስ 21 የሚሆኑት እንደ ዋሊያ፣ ቀይ ቀበሮ፣ የጭላዳ ዝንጀሮ፣ የሚኒሊክ ድኩላና ሌሎች የዱር እንስሳት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም “… አባይ ዳር ነው ቤቴ፣ ጣና ዳር ነው ቤቴ- አሳ አበላሻላሁ እንደ ድህነቴ” እያለ ጉብሉ ሁሉ ለሚወዳትና ለሚያፈቅራት በዱር፣ በሸንተረርና በገደሉ ሁሉ ሲዘፍን የሚውለው። በጣና ሃይቅና አባይ ወንዝ አካባቢዎች ለሚገኙ ማህበረሰቦች ምን ቢያጡና ቢቸገሩ ከቤታቸው የአሳ ስጋ እንደማይጠፋ ማሳያ መሆኑን ስነ ቃሉ ያመላክታል። ድሮ የድሃ ምግብ የነበረው አሳ አሁን አሁን ደግሞ የዘናጭ ሃብታም ምግብ ብቻ ሆኗል። ለምን የሃብታም ምግብ ብቻ ሆነ የሚለውን በዚህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ ለመጥቀስ ይሞከራል። ከሃይቁ 13 ሺህ ቶን የአሳ ምርት በማምረት መጠቀም እንደሚቻል ሰምተዋል? ለነገሩ አለ መባሉ ምን ጥቅም አለው። እስካሁን በአሳ አስጋሪዎች እየወጣ ጥቅም ላይ የሚውለው ከአንድ ሺህ ቶን ያልበለጠ መሆኑን ሲሰሙና ሲያዩ ደግሞ ቁጭትና ጸጸት ይፈጥራል። ያለንን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ አልምተን አለመጠቀማችን አንዱ ማሳያ ነው። የአሳ ሃብቱን በስፋት በማልማት አስግሮ መጠቀምና ወደ ውጭ መላክ ቢቻል ኖሮ አሁን ላይ ያለውን ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን ዶላር ከዘርፉ የሚገኝ ገቢ በብዙ እጥፍ ማሳደግ ይቻል እንደነበር መገመት አያዳግትም። ምንም እንኳ ተመራማሪዎችና ጸሃፍት ከላይ የጠቀስኳቸውን ማስረጃዎች ጠቅሰው ቢጽፉና በጥናታቸው ቢያመላክቱም አሁን አሁን በጣና ሃይቅ ላይ የተጋረጠው የመጤ አረም አደጋ ማስረጃውን ተረት ተረት እንዳያደርገው የሚያሰጋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በጎንደር ዘሪያ ወረዳ የሻጎ መንጌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ፈንታሁን ውቤና መንጌ አዱኛ የሚያረጋግጡት ይህን ነው። ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ እንደሚባለው እምቦጭ የተባለው መጤ አረም የተከሰተው በ2004 ዓ.ም አከባቢ መሆኑን ያወሳሉ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ በደንገልና ታንኳ ሃይቁ ውስጥ በመግባት አሳ በማጥመድ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ከመመገብ አልፈው በቋንጣ መልክ እያዘጋጁ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ይሰጡ እንደነበር ተናግረዋል። የዛሬን አያርገውና ከዛም አልፎ ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ያገኙ ነበር። ፓፒረስ፣ ጨፌና ሌሎች የሳር ዝርያዎች በሃይቁ ዳር ለዳር በብዛት ይበቅል ስለነበር እያጨዱ ለከብቶቻቸው መኖ በማቅረብ ሳይቸገሩ ይኖሩ እንደነበር ጠቅሰዋል። “ከጣና ዳር የሚታጨደውን ሳር የበሉ ላሞች ወተታቸው የተትረፈረፈ ነበር” በማለት በቁጭት ስሜት መሬት መሬቱን እያዩ ይገልጻሉ። ከብቶቻቸውን ከሃይቁ ያጠጣሉ። ልብሳቸውን ያጥባሉ። ይዋኛሉ። ይታጠባሉ ። አሁን ላይ ግን ሁለ ነገራቸው ከጣና ሐይቅ የተዛመደ እንደነበር በጸጸት ስሜት በትዝታ ያወሳሉ ። ወደ አጎራባች ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሚያደርጉት ጉዞ እንኳን በደንገልና ታንኳ በመጠቀም ያለምንም ድካምና የጸሃይ ቃጠሎ በሃይቁ ላይ ይጓጓዙ እንደነበር ነው የሚያወሱት። ይህ የተረገመ መጤ አረም በመምጣቱ ግን ዛሬ ላይ ተረት ተረት መስሎ እየታየን ነው ይላሉ አርሶ አደሮቹ። ከጥቂት ቀናት በፊት የእምቦጭ አረሙ እዚህ ጫፍ ላይ ብቻ ነበር። “እኛም እሰይ ሊጠፋልን ነው። ይህስ ባሉት ማሽኖች በአንድ ሳምንት ማጽዳት ይቻላል። እኛም በጉልበታችን እናግዛለን ብለን ተስፋ አጭሮብን ነበር። ዛሬ ላይ ደግሞ ከየት እንደመጣ ሳይታወቅ ዓይን ማየት እስከሚችለው የርቀት ጥግ ድረስ ሃይቁ በመጤ አረሙ ተሸፍኗል ሲሉ በምሬት ይገልፃሉ ። በውሃው ሞገድ ከሌላ አካባቢ ተገፍቶ ወደዚህ በመምጣቱ ሃይቁን ማየት ከማንችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል። አንድ ሳምንት ጠፋ ስትል በቀጣዩ ሳምንት ሸፍኖት ታገኘዋለህ። የመራባት አቅሙም ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት የሚጨምር በመሆኑ አስቸጋሪ ነው” በማለት ገልጸውታል። ወዲያው እንደተከሰተ በጉልበታችን አረሙን ለማስወገድ ያላደረግነው ጥረትም አልነበረም። ህጻን፣ ወጣት፣ ሴቱ ወንዱ… ጧት ጀምሮ እስከ ማታ ውሎው አረሙን በማውጣትና በመቆለል ነበር ጊዜውን ያሳለፈው። ከሁለትና ሶስት ዓመታት ወዲህ አረሙ እየገነገነ፤ የእኛ ጉልበት ደግሞ እየደከመ መጣ። ትልቅ ጠላት ነው የመጣብን። ከጠላትም ታግለህ የማታሸንፈው ሰይጣናዊ ጠላት ነው ። ጊዜ የማይጥለው ፣ ጊዜ የማይከዳው ብርቱ ጠላት ነው ያጋጠመን በማለትም የአረሙ አስቸጋሪነት ይገልፁታል ። የውጭ ወራሪን ፊት ለፊት ተጋፍጠህ ገለህና ሞተህ ታሸንፈዋለህ። እምቦጭ ግን ከውጭ ጠላት በላይ በመሆኑ ለመንግስት አቤት ማለታችን ከመቀጠል ውጪ አማራጭ አጥተንበታል ። መንግስትም የኛን አቤቱታና የምሁራኖችን ሃሳብ በማዳመጥ የተለያዩ ጥረቶችን ለማድረግ ሞክሯል። አረሙን የሚነቅሉ ማሽኖች ቢያስገባም ችግሩ ምን እንደሆነ ባናውቅም በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ ነው ለማለት ተቸግረናል። የባለሙያዎች ችግር ያለ ይመስለናል። በሆነ ባልሆነ ሰበብ እየፈጠሩ ከሚሰሩበት ይልቅ የማይሰሩበት ጊዜ ይበልጣል በማለት አርሶ አደሮቹ ያደረባቸውን ስጋት ያብራራሉ። “አታዩትም በማዳበሪያና በመስመር የዘራነው ሰብል እኮ እንደዚህ ለምልሞና አምሮ አይታይም” አሉ ጣታቸውን በእምቦጭ አረም ወደ ተወረረው የጣና ሃይቅ እያመለከቱ። አሁን ስጋታችን የኛ የአሳ፣ የወተት፣ ውሃ የመቅዳትም ሆነ እንስሳትን የማጠጣት… ሌሎች ጥቅሞች ቀሩብን ሳይሆን የጣና ሃይቅን በማድረቅ አካባቢያችን ወደ ምድረ በዳነት እንዳይቀይረው ነው የምንሰጋው ብለዋል ። በጣና ሃይቅ የተከሰተውን እምቦጭ የተባለ መጤ አረም ለማስወገድ ሰባት ማሽኖች በሽጎ መንጌ ቀበሌና ጎርጎራ አካባቢዎች ገብተው እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የጣና ሃይቅ ፕሮጀክት ከፍተኛ መካኒክና አስተባባሪ መሃመድ ሃሰን ነው። አንዱ ማሽን በጎርጎራ በኩል ሲሆን ቀሪዎቹ በሸጎ መንጌ ነው የሚገኙት። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከሙላት ኢንጅነሪንግ ያሰራትን ጨምሮ አማጋና ካናዳ የተባሉ ሶስት የመጤ አረሙን እየነቀሉና የሚያጓጉዙ ማሽኖች አሉ። አንድ ከመሬት የተገጠመና ሁለት ደግሞ በበጋ ወቅት ውሃው ሲሸሽ ተቀጣጥለው ማሽኖቹ የነቀሉትን አረም ተቀብለው የሚያጓጓዙ ተጨማሪ ማሽኖች አሉ። አንድ ስካቬተርና ሲኖትራኮችም አረሙን ወደ ማስወገጃ ቦታ ለማድረስ የሚሰሩ አሉ። አማጋ የተባለችው ማሽን ከሁሉም ፈጣንና የነዳጅ ፍጆታዋም በአራት ሰዓት ከ25 ሊትር የማይበልጥ ነው። በአማጋ ስፖንጅ ፋብሪካ ከቻይና ተገዝታ መምጣቷን የመካኒክ ባለሙያው ተናግሯል። በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያመጧት ካናዳ የተሰኘችው ማሽን ደግሞ የነዳጅ ፍጆታዋ ከፍ ያለና አረም የማስወገድ አቅሟ ደግሞ ዝቅ ያለ ነው - ከአማጋ ጋር ስትነጻጸር። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲና ሙላት ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ የተሰራው ማሽን ደግሞ አረሙን በማጓጓዝ ከሃይቁ አርቆ በማስወገድ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ማሽኖችን አቀናጅቶ በሙሉ አቅማቸው ለማሰራት የገጠመን ዋናው ችግር ለማሽኖች ማደሪያ የሚሆን ወደብ አለመኖሩ ነው። በዚህም የውሃው ሞገድ ሲጨምር ማሽኖቹን ገፍቶ ወደ የብሱ አውጥቶአቸው ያድራል። ወደ የብሱ የተገፉት ማሽኖች ከድንጋይ ጋር በመጋጨት ብልሽት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ጧት ስራ ለመጀመር ሲታሰብ ሁሉንም ማሽኖች ተራ በተራ ወደ ሃይቁ ውሃማ ክፍል በስካቬተር ተገፍተው ይገባሉ። አንዳንዱ አካባቢ ለስካቬተር እንቅስቃሴም አስቸጋሪ በመሆኑ ችግር እያጋጠመን ነው ሲል ባለሙያው ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም የማሽኖቹ የማስተግበሪያ ሰነድ/ማንዋል/ የላቸውም። የባለሙያዎች የደህንነት ልብስ፣ መድሃኒትና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች አለመሟላት ሌላው እያጋጠማቸው ያለ ችግር። ከሁሉም በላይ ግን ለማሽኖቹ የሚያገለግለው መለዋወጫ ዕቃ ከውጭ የሚመጣ በመሆኑ በቀላል ብልሽት እስከ አራት ወርና አምስት ወር የሚቆሙ ማሽኖች አሉ በማለት አርሶ አደሮቹ ያነሱትን ቅሬታ ትክክለኛነት አረጋግጠዋል። ከሙላት ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር የተመረቱት ማሽኖች የአካባቢውን ስነ ምህዳር፣ አየር ጸባይና የችግሩን ስፋት መሰረት አድርገው የተመረቱ በመሆናቸው የእምቦጭን አረም በማስወገድ ችግር እንደሌለባቸው በባህርደር ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተቋም መምህርና የጣና ፕሮጀክት ቴክኒካል ቡድን መሪ አቶ ዮናስ ምትኩ ይናገራሉ። የማሽኖቹ በአካባቢው መመረትም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ ለተማሪዎች የተግባር ማስተማሪያ በማድረግ የእውቀትና ክህሎት ማበልጸጊያ ሆኖ ማገልገሉን ጠቅሰው መንግስትም ለአገር ውስጥ አምራቾች ትኩረት እንዲሰጥ በተግባር ያሳየንበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል። የአረም ማጨጃ ማሽኗ በቀን አንድ ሺህ ሜትር ኩብ እምቦጭ መንቀልና ማጓጓዝ የምትችል ናት። ብልሽት እንኳ ቢያጋጥማት በሰራው ድርጅትና በራሳችን ባለሙያዎች በቀላሉ በመጠገን ወደ ስራ በማስገባት ለግማሽ ቀን እንኳ እንዳይቆሙ የሚያደርግ ነው። 80 ሜትር ኩብ በአንድ ጊዜ የሚያጓጓዙ ሁለት ማሽኖችን በመሬት ከተገጠመው ጋር በመቀጣጠልም ወደ ሃይቁ የውስጥ ክፍል በመግባት አረሙን ማስወገድ የሚቻልበት እድል አለ ብልዋል። ከውጭ የመጡት ማሽኖች ዋና ችግራቸው አረሙን አጽድተው ከውሃው ዳር ነው መልሰው የሚደፉት። ይህ ደግሞ ማዕበል ሲመጣ ተመልሶ በመግባት ይራባል። ዳር ላይ ቢደርቅ እንኳ እየገባ ደለል በመሆን ለሃይቁ ስጋት መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ በአገር ውስጥ ከተመረተው የመጓጓዟ ማሽን ጋር በማቀናጀት በርቀት ወስዶ በማስወገድ የተወገደው አረም ዳግም ለሃይቁ ስጋት እንዳይሆን ማድረግ ይቻላል። የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ልየው በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ለጣና ሃይቅ ጥበቃ ትኩረት በመስጠቱ እስከ አሁን ድረስ በአካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር፣ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ተቋማት ሲከናወን የነበረውን የእንቦጭ አረም ማስወገድ ተግባር አቀናጅቶ  መምራት እንዲቻል ኤጀንሲያቸውን መቃቋሙን ይናገራሉ። ከአንድ ወር ያልበለጠ ጊዜ ያለው ኤጀንሲው በውሃ አካላት ተፋሰስ ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎችን በመስራት ፣ በመጤ አረም የተወረሩ ሃይቆችን ከአረሙ የጸዱ ማድረግና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ መከላከል ፣ ለመጤ አረም ምግብ በመሆን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥረውን የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ሃይቆቹና ሌሎች የውሃ አካላት እንዳይገባ መከላከልና በውሃ አካላት ያለውን ብዝሃ ህይወት መጠበቅ ላይ አተኩሮ ለመስራት አቅዶ እንቅስቃሴ ጀምሯል ። ኤጀንሲው ገና ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተው እምቦጭ የተባለውን መጤ አረም የት የት አካባቢ በብዛት እንደሚገኝ፣ ምን ያህል የሃይቁን ክፍል እንደሸፈነና አረሙን ለማስወገድ የሚያስፈልገውን ገንዘብና የሰው ሃይል የሚያጠኑ ባለሙያዎች ተመድበው የዳሰሳና ቅኝት ጥናት በማካሄድ መረጃ የመሰባሰብ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል። ምን ያህሉ የሃይቁ ክፍል በእምቦጭ ተወሯል የሚለውን በትክክል ለመግለጽም የተሰበሰበውን መረጃ በሳይንሳዊ መንገድ የመተንተን ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። መጤ አረሙ በሃይቁ ላይም ሆነ በአካባቢው በሚኖረው ማህበረሰብ ላይ እያደረሰ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ በያዝነው በጀት ዓመት በሰው ሃይልና በመካኒካል ዘዴ ለማስወገድ ርብርብ ይደረጋል። ከዚህ ውስጥም ትኩረት የምንሰጠው በመጀመሪያ በሰው ሀይል ተጠቅመን ለማስወገድ ነው። በዚህም በጣና አዋሳኝ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ከ80 ሺህ በላይ ህዝብ በነጻ በማሳተፍ ከህዳር 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከ30 እስከ 45 ቀናት በሚካሄድ የዘመቻ ስራ ለማከናወን የቅድም ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው። በበጀት ዓመቱ አረሙን ለማስወገድ በእቅድ ከተያዘው ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን በሰው ሃይል ለማስወገድ ግብ ተይዟል። በማሽነሪ በመጠቀም ደግሞ 20 በመቶ የሚሆነው እምቦጭ ይወገዳል። ለዚህም ከሰባቱ ማሽነሪዎች በተጨማሪ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያመረታት ማሽን ወደ ስራ ለማስገባት መታቀዱን ተናግረዋል። በሃይቁ የሚገኙ ሁሉንም ማሽነሪዎች በማቀናጀት ወደ ስራ ለማስገባት ቴክኒካል ኮሚቴ በማቋቋም ርክክብ እንደሚደረግ ጠቁመው የመለዋወጫ እጥረትን ለመቅረፍ ከአገር ውስጥ አምራች ድርጅቶች ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል። ለዚህም ከአማራ ብረታ ብረት ድርጅት ጋር በቅርበት መስራት ከተጀመረበት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚጠየቀውን የማሽኖች መለዋወጫ ዕቃ በአጭር ጊዜ ሰርቶ ማቅረብ ችሏል። በቀጣይም ቅንጅታዊ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥል። መጤ አረሙ እያደረሰ ያለው ጉዳት በወቅታዊ የፖለቲካ ውጥረት እየተረሳ ነው ለሚለው ጥያቄ ግን  አቶ ዘላለም አይቀበሉትም። እንዳውም አሁን ነው ትኩረት የተሰጠው ባይ ናቸው። ምክንያቱም እስካሁን ራሱን ችሎ የሚሰራ ባለቤት የሆነ ተቋም አልነበረውም። አሁን ግን የክልሉ መንግስት በኤጀንሲ ደረጃ ተቋም አቋቋሟል ብለዋል። አሁን ያለው ሌላው ችግር የወደብ ጉዳይ ነው። ወደብ ባለመኖሩ ማሽኖች በማዕበል እየተገፉ ዳር በመውጣታቸው ለብልሽት እየተዳረጉ ነው። እስካሁንም ወደቡ መገንባት ነበረበት። የት ላይ ይገንባ የሚለውን በባለሙያ በማስጠናት ወደቡን ለመገንባት እንጥራለን። መስሪያቤታችን የተቋቋመውም ይህን ችግር በመፍታት የእምቦጭ መጤ አረምን ለማስወገድ ነው። እምቦጭን ለማጥፋት ሌላኛው አማራጭ ኬሚካል መጠቀም ነው። ነገር ግን የጠና ሃይቅ ጥልቀት ቅርብ ከመሆኑና ካለው ሰፊ ብዝሃ ህይወት አንጻር በኬሚካል እምቦጭን የማጥፋት ተግባር የአረሙ ብስብሳሽ በመስመጥ ሃይቁ ውስጥ ላይ በማረፍ በደለል በቀላሉ እንዲሞላ ስለሚያደርግ ተመራጭ እንዳልሆነ ኤጀንሲው አስታውቋል። በመጀመሪያ በላቲን አሜሪካ መነሻውን ያደረገው እምቦጭ ዛሬ ላይ በኒውዝላንድ፣ፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ካምቦዲያ፣ ሉዊዚያና አሜሪካ፣ በህንድ፣ በኢትዮጵያ፣ ማላዊና ግብጽ የሚገኙ የውሃ አካላትን በመውራር ብዙ ጥፋት እያደረሰ የሚገኝ አደገኛ አረም መሆኑ የሚተወቅ ነው። በእኛ ሀገር ደግሞ ከጣና በተጨማሪ በቆቃና በሌሎች የውሃ አካላት መስፋፋት ጀምሯል ። እውነት ይህ በሰይጣን የተመሰለው መጤ አረም ተወግዶ አርሶ አደሩ እፎይታ ያገኝ ይሆን? ምን ይህ ብቻ በናይል ተፋሰስ የሚኖረው ከ200 ሚሊየን በላይ የሚቆጠር ህዘብስ የ60 በመቶ ውሃ መገኛው የጣና ሃይቅ የተጋረጠበትን አደጋ ተቀልብሶ እናየው ይሆን? አዲስ የተቋቋመው ኤጀንሲ እቅዱና ህልሙ ተሳክቶ የእምቦጭን መጥፋት ያበስር ይሆን ወይስ ልክ እንደ እስከ ዛሬው ሪፖርት ይህን ያህል በመቶ ለመቀነስ፣ ቀነስን… የሚለውን ውሃ የማይቋጥር መረጃ እየተሰጠ ይቀጥል ይሆን። ዋናው ነገር ሰላም፣ ዋናው ነገር ጤና ያለው ዘፋኝ ማን ነበር። ጤና ሰጥቶን እናየዋለን።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም