ለአማራና ቅማንት ህዝቦች የሚበጀው ያላቸውን ጥያቄ በውይይት መፍታት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

201
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 11/2012 ለአማራና ቅማንት ህዝቦች የሚበጀው ያላቸውን ጥያቄ በውይይት መፍታት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመለከቱ። የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያስተላለፉት የመንግስት ዕቅድና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል የአማራና ቅማንት ጉዳይ ሲሆን አሁን እየተነሱ ያሉ ጉዳዮች መንግስት እንዴት ለመፍታት አስቧል? የሚል ሀሳብ ተነስቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራና ቅማንት ህዝቦች ለረጅም ዓመታት አብረው የኖሩና ጠንካራ ትስስር ያላቸው እንደሆነ አውስተዋል። በአሁኑ ሰአት በአማራና ቅማንት ጉዳይ ለተነሱ ጥያቄዎች የአማራ ክልል ምላሽ እየሰጠ መሆኑንና አሁን የቀረው የሶስት ቀበሌዎች ጥያቄ እንደሆነ ገልጸዋል። በጎንደር ከህዝቡ ጋር ውይይት እንዳደረጉና በቢሯቸው ከአማራና ቅማንት የአገር ሽማግሌዎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል። ለሁለቱ ህዝቦች የሚበጀው መገዳደል ሳይሆን ያሉትን ጥያቄዎች ለመፍታት ቁጭ ብለው መነጋጋገር እንዳለባቸው አመልክተዋል። የአማራና ህዝብ ቅማንት ህዝብን በማጋጨት በግጭት ውስጥ ማትረፍ የሚፈልጉ ሰዎች ለጊዜው ይሆናል እንጂ ሁለቱን ህዝቦች ለዘላለም መለየት እንደማይቻል ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት። ችግሩን ለመፍታት ሁሉም አካላት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። ''ሰላምን ለማምጣት ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲኖር አበክሮ መስራት ይገባልም'' ብለዋል። የፌዴራል መንግስት የአማራ ክልል መንግስት ባቀረበው ጥያቄ አማካኝነት ጣልቃ ገብቶ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት እየሰራ እንደሆነና ውጤቱም በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚታይ አመልክተዋል። ሰው የገደሉና ጉዳት ያደረሱ አካላት ለህግ እንደሚቀርቡ ገልጸው፤ ህዝቦችን ለማጣላት የሚሰሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም