የእደ ጥበብ ውጤቶች ማምረቻ ማእከላት እንዲቋቋሙ ድጋፍ ይደረጋል - የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት

298
ጎንደር ሰኔ 11/2010 በሀገሪቱ ታላላቅ የቱሪስት የመዳረሻ አካባቢዎች የሀገሪቱን ባህላዊ እሴቶች የሚያስተዋውቁ የእደ ጥበብ ውጤቶች አምራች ማእከላት እንዲቋቋሙ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አስታወቀ፡፡ በጎንደር ከተማ ፋሲል መዋኛ ቅጥር ግቢ በድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ ላለፉት 15 ቀናት በተለያዩ የእደ ጥበብ ሙያዎች የሰለጠኑ 55 ሰልጣኞች ትናንት የእውቅና ምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡ የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር የቻለ ምህረት እንደተናገሩት በሀገሪቱ ታላላቅ የቱሪስት መዳረሻ በሆኑት በጎንደር፣ በአክሱምና በሀረር አካባቢዎች 12 የእድ ጥበብ ውጤቶች ማምረቻ ማእከላት ተቋቁመዋል፡፡ በማእከላቱ የሀገሪቱን ባህልና እሴቶች የሚያንጸባርቁና ለውጪ ቱሪስቶች ለማስተዋወቅ የሚረዱ የባህላዊ አልባሳት፣ ቅርጻ ቅርጽና የስእል ስራዎች በእደ ጥበብ ባለሙያዎች ተመርተው ለቱሪስቶች በመቅረብ ላይ ናቸው፡፡ ድርጀቱ ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ ከ100 በላይ የእድ ጥበብ አምራቾች በማህበር ተደራጅተው በሽመና፣ በጥልፍ፣ በሸክላ ስራ፣ በቅርጻ ቅርጽና ስእል ስራዎች ሰልጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ማእከላቱ የአካባቢውን የእድ ጥበብ አምራቾች ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ኑሮአቸውን ለማሻሻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከእንጨትና ከነሀስ ተሰርተው ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ የአካባቢያችን ወካይ የታሪክና የቱሪዝም ቅርጻ ቅርጾችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ረገድ የእደ ጥበበ ማምረቻ ማእከላቱ ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው ''የእድ ጥበብ ማምረቻ ማእከላቱ ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማምረቻና መሸጫ ቦታ ጀምሮ የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻቻል'' ብለዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ በድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ 55 ባለሙያዎች በሽመና፣ በጥልፍ፣ በሸክላና በቅርጻቅርጽ ስራ የሁለት ሳምንት የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትን ለመጎብኘት በየአመቱ ከ70ሺ ያላነሱ የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቶች ወደ ከተማው የሚመጡ ሲሆን ህብረተሰቡ ከቱሪዝም ገቢው እስከ 220 ሚሊዮን ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በድርጅቱ ድጋፍ ስልጠናውን ከወሰዱ የእደ ጥበብ ባለሙያዎች መካከል የባህላዊ የጥልፍ ስራ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ጥበብ በለጠ ''ስልጠናው ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ምርት ለቱሪስቶች ማቅረብ እንድችል በቂ የተግባር ስልጠና አግኝቻለሁ'' ብላለች፡፡ የሽመና ባለሙያው ወጣት ኑሬ እስማኤል በባህላዊ የሽመና መሳሪያ ሦስት ሰአት የሚፈጅብኝን የጥበብ ስራ በዘመናዊ የሽመና መሳሪያ በ15 ደቂቃ ውስጥ መስራት እንደሚቻል በስልጠናው በቂ ክህሎት መጨበጥ ችያለሁ ሲል ተናግሯል፡፡ በእለቱ ከተለያዩ የእደ ጥበብ ማምረቻ ማእከላት ተውጣጥተው ስልጠናው ለወሰዱ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች የእውቅና ምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን በሰልጣኞች የተመረቱ የእደ ጥበብ ምርቶችም በእንግዶች ተጎብኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም