የሰሜን ሸዋ ዞኗ ሲያደብርና ዋዩ ዛሬ የአርሶ አደሮችን ቀን ታስተናግዳለች

45
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 11/2012 በሰሜን ሸዋ ዞን በሰብል ምርታማነቷ የምትታወቀው ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ዛሬ አገር አቀፍ የአርሶ አደሮችን ቀን ታስተናግዳለች። በግብርና ሚኒስቴር በተዘጋጀው የአርሶ አደሮች ቀን የምርምር ተቋማት፣ የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ የዘር ብዜት አቅራቢ ድርጅቶችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል። ከደብረብርሃን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ከቆዳ ስፋቷ 50 በመቶው በሰብል የሚሸፈን ነው። በ2011/2012 የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው 21 ሺህ ሄክታር መሬቷ ከ877 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የወረዳው ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አከበረኝ ዓለሙ ለኢዜአ ተናግረዋል። ስንዴ፣ ጤፍ፣ ምስርና ሌሎች ሰብሎች በኩታ ገጠም የተዘራ ሲሆን በዋናነት በኩታ ገጠም ከተሸፈነው ስምንት ሺህ ሄክታር የስንዴ ማሳ ከ533 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል። በአፈር ማዳበሪያ፣ በፀረ-ተባይ መድሃኒት፣ በተሻሻለ ምርጥ ዘርና በዘመናዊ አስተራረስ ዘዴ በመጠቀም ማሳዎችን በሰብል ለመሸፈን ጥረት መደረጉንም አቶ አከበረኝ ገልፀዋል። ዛሬ በሚካሄደው የባለድርሻ አካላት ውይይት አርሶ አደሮች በሚያነሷቸው የምርት መሰብሰቢያ ቴከኖሎጂ፣ የገበያ ትስስርና መሰል ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ምክክር እንደሚደረግም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም