ኢትዮጵያ በ2030 ያለእድሜ ጋብቻን ለመግታት እያደረገች ያለውን ጥረት ለማሳካት በስድስት እጥፍ መጨመር አለባት

55
ጥቅምት 10/2012 ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2030 ያለእድሜ ጋብቻን ለመግታት አሁን እያደረገች ያለውን ጥረት በስድስት እጥፍ መጨመር እንዳለባት ተገለጸ። የገንዘብ ሚኒስቴርና የተመድ ህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዛሬ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ያለእድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የተሰራ ስራ ቢኖርም ብዙ የሚቀር የቤት ስራ አለ። በመግለጫው እንደተመለከተው እ.አ.አ በ2005 ስልሳ በመቶ የነበረውን ያለእድሜ ጋብቻ ከ10 ዓመት በኋላ 40 በመቶ ማድረስ የተቻለ ቢሆንም በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ጥረቱን በስድስት እጥፍ ማሳደግ ይገባል። ያለ እድሜ ጋብቻን በተመለከተ አሁን ባለው ሁኔታ እንኳ 15 ሚሊዮን ያህሉ ህጻናት ያለ እድሜ ጋብቻ የሚፈጽሙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 6 ሚሊዮኖቹ ከ15 አመት በታች እንደሆኑ ተገልጿል። በጤና ሽፋን፣ በንጹሁ ውሃ አቅርቦት፣ በህጻናት ጤና አጠባበቅ፣ በምግብ አቅርቦትና በንጽህና ላይ ባለፉት ጥቂት አመታት የተሻሻሉ ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች  ቢኖሩም አገሪቷ አሁንም በዘርፉ ብዙ ልትሰራ እንደሚገባ መግለጫው ጠቁሟል። በትምህርት የ1ደኛ ደረጃ ሽፋን እየተስፋፋ ቢሆንም ወደ 2ተኛ ደረጃ የሚሸጋገሩት ጥቂቶች ብቻ መሆናቸውንና የተቀሩት ትምህርታቸውን እንደሚያቋርጡ ተገልጿል። ለዚህም እንደ ምክንያት የተነሱት፣ በጋብቻ በአቅም እጦት፣ በትምህርት ቤት መራቅና የመሰረተ ልማት አለመመቻቸት፣ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በዚህ ሳቢያ እድሜያቸው ከ7 እስከ 14 የሚሆኑ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህጻናት በትምህርት ገበታ ላይ እንደማይገኙ መግለጫው አመላክቷል። በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አዴሌ ኮደር በኢትዮጵያ በህጻናትና ሴቶች ላይ እየተሰሩ ያሉ ጅምሮች ቢኖሩም፣ አሁንም በለጋ እድሜ ባሉት ላይ መዋዕለ ነዋይ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። በለጋ እድሜ በሚገኙ ህጻናት ላይ የሚደረገው መዋለ ነዋይ የእውቀት አድማሳቸውን ለማስፋትና በህይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ በመሆኑ ርብርብ ይሻል ብለዋል። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ በበኩላቸው መንግስት ከአጠቃላይ የአገሪቷ በጀት 30 በመቶውን ለትምህርትና ለጤና እንደሚያውል አንስተዋል። ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን አንስተው በቀጣይ ለማሳካት የሚጠበቁትን ግቦች ከዳር ለማድረስ የአጋር አካላትን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጸዋል። መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በተለይ ያለእድሜ ጋብቻ እንዲቀርና ሴቶች በትምህርት እንዲቀጥሉ ለማስቻል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽነት ላይ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የእናቶችና የህጻናት ሞት እንዲቀንስ በጤናው ዘርፍ ጠንክሮ እንዲሰራና ኢትዮጵያ በ2030 ለመድረስ ያስቀመጠቻቸውን ግቦች ለማሳካት ያላሳለሰ የጥረት እንደሚጠይቅ በጋራ መግለጫው ምክረ ሃሳብ ተሰጥቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም