የትግራይና የአፋር የሰላም ኮንፈረንስ በአላማጣ ከተማ ተካሄደ

112
ማይጨው 10 ቀን 2012 የትግራይና የአፋርን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የሰላም ኮንፈረንስ በአላማጣ ከተማ ተካሄደ። በራያ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ክልሎቹን በመሠረተ ልማት አውታሮች ለማስተሳሰር ትኩረት እንደተሰጠው ተመልክቷል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ እንደተናገሩት"ከአባቶቻችን ከአያቶቻችን የወረስነውን ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ዛሬ ላይ ልናጎለብተው  ይገባል።" የአገር ውስጥ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በማዳበር፣ ይዘታቸውን ሳይለቁና ሳይበረዙ ዘላቂ  ሰላምና እድገት  ለማምጣት  በጥናት ተደግፈው ለትውልድ መተላለፍ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል። ለዘመናት በቋንቋ፣ በባህልና በሃይማኖት የተሳሰሩት የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች ሰላማቸውን በጋራ በመጠበቅ ዘላቂ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች አስታውቀዋል። ከአፋር ክልል መጋሌ ወረዳ የመጡት ሐጂ ጀናቱ መሐመድ  የትግራይና የአፋር ሕዝቦች በጉርብትና ብቻ ሳይሆን፣ በደም የተሳሰሩና ለአንድ ዓላማ መስዋዕት የከፈሉ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ኮንፍረንሱ በክልሎቹ አስተማማኝ ሰላም  ለማምጣትና በልማት ላይ ለመወያየት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። የአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የግጭት መከላከልና አፈታት ዳይሬክተር አቶ ኡስማን  ኢንሀባ  በበኩላቸው  በክልሎቹ መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ልማቱን በጋራ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። የቆየ ጠንካራ የሆነ የሕዝብ ግንኙነት በመኖሩ ለዘመናት ሰላማቸውን ማስጠበቅ ችለዋል’’ ያሉት ደግሞ በትግራይ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ የሰላምና ብዘሃነት አያያዝ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ካልአዩ አሰፋ ናቸው። ''የሁለቱም ክልል ሕዝቦች ደስታችን ይሁን ሀዘናችንን በጋራ እየተካፈልን ነው የመጣነው'' ያሉት ደግሞ  ከትግራይ ክልል የራያ አዘቦ ወረዳ የኮንፍረንሱ ተሳታፊ  አቶ ኪሮስ አውሮ ናቸው። የሕዝቦቹ አንድነትና ትብብር መጠናከር እንዳለበትም አስታውቀዋል። በኮንፍረንሱ ከ200 በላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም