የአፍሪካ ሴት መሪዎች ኔትወርክ የኢትዮጵያ ምዕራፍ ተመሰረተ

187
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 10/2012 የአፍሪካ ሴት መሪዎች ትስስር በኢትዮጵያ ‘’የኢትዮጵያ ምዕራፍ’’ በሚል ዛሬ በአዲስ አበባ ተመስርቷል። በምስረታው ወቅት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሴቶችን መብትና ጥቅም የሚያስከብር ጠንካራ ድርጅት ያስፈልጋል። ዛሬ የተመሰረተው ትስስር ሴት መሪዎች ችግሮቻቸውን በጋራ እንዲፈቱና ለአገራቸው ብሎም ለአፍሪካ ሴቶች መብት መከበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ያግዛል። በተለይ ወደ መሪነት ሲመጡ ድርብ ሃላፊነት ያለባቸው ሲሆን፤ አሁን የተመሰረተው የትስስሩ የኢትዮጵያ ምዕራፍ ሴቶችን በማብቃትና ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑ ለማሳለጥና ችግሮችን በቀላሉ ለማለፍ እንደሚያስችል ጠቁመዋል። ''ይህንን ትስስር ኢትዮጵያውያን ሴት መሪዎች ለሌሎች አገሮች ሴቶች በምሳሌነት መመራትና ስራቸውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናል'' ብለዋል። በኢትዮጵያ በከፍተኛ የሃላፊነት እርከን ላይ ያሉ ሴቶች ፉክክር ሳይሆን መተባባርን መርህ አድርገው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። አሁን በተግባር እየታየ ያለው በተናጥል የሚደረግ ጥረትና ፉክክር ወደ መልካም ትብብርና አንድነት ማምጣት እንደሚጠበቅ ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል። መንግስት ሴቶችን ወደ አመራር ሰጪነት ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝና የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ብርቱ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል። የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋይ በበኩላቸው  የትስስሩ የኢትዮጰያ ምዕራፍ መመስረት ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት የተጀመሩ ስራዎችን ለማስቀጠል የሚያግዝ እንደሚሆን ገልጸዋል። ''ሴቶች ድርብ ሃላፊነታቸውን በተለናጠል ለማስቀጠል ከመጣር ይልቅ በጋራ ለችግሮች መፍትሄ ለማበጀት ጠቀሜታው የጎላ ነው'' ብለዋል። በአፍሪካ በ2063 ሴቶች በተመለከተ የተያዘውን አጀንዳ ለማሳካት የጋራ ጥረቱ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። የትስስሩ መመስረት ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ በብዛትና በጥራት ሴት አመራሮችን ማፍራት  መሆኑን ጠቁመዋል። ''የአፍሪካ ሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት ከአገር አልፎ በአፍሪካ ደረጃ በጋራ ለመፍታት ያስችላል'' ብለዋል። በምስረታው ወቅት ሴት ሚኒስትሮች፣ የክልል ተወካዮችና ታዋቂ ሰዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጨምሮ የአፍሪካና የሌሎች አገሮች ተወካዮች ተገኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም