በሩብ አመቱ ከ723 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከወጪ ንግድ ገቢ ተገኘ

77
ጥቅምት 10/2012 በተያዘው በጀት አመት የመጀመሪያው ሩብ አመት ከወጪ ንግድ ከ723 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ለኢዜአ እንደተናገሩት በመጀመሪያው ሩብ አመት ከወጪ ንግድ 707 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 723 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። አፈጻጸሙ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 628 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸርም የ95 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል። የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቡና፣ የኬሚካልና ግንባታ ግብአቶች ደግሞ በሩብ አመቱ ከተያዘላቸው እቅድ ከ75 እስከ 90 በመቶ በማሳካት የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የቅባት እህሎች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ባህር ዛፍ፣ የቁም እንስሳ፣ ሰም፣ ስጋና ታንታለም ግን ከ50 እስከ 75 በመቶ እቅዳቸውን አሳክተዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ለአፈጻጸሙ መሻሻል የወጪ ንግድን ገቢ ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ቅንጅታዊ ስራዎችና እየወጡ ያሉ መመሪያዎች አስተዋጽኦ አድርገዋል። የወጪ ንግድ አንዱ እንቅፋት የሆነውን ኮንትሮባንድ በመከላከል በኩልም ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላችውን አክለዋል። የኮንትሮባንድ መውጫ በሮችን በማጥበብና መዝጋት በተሰሩት ስራዎች ለአብነትም በኬንያ በኩል ቀይ ቦሎቄ፣ ማሾና ሌሎች ይወጡ የነበሩ የወጪ ንግድ ምርቶች መቆጣጠር እየተቻለ ነው ብለዋል። ሌሎች የወጪ ንግድን የሚያዳክሙ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከልም ከገቢዎች ሚኒስቴርና ሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት። በአገር ውስጥ ያለውን ህገ ወጥ የንግድ ስርአት ወደ ህጋዊ በማምጣትና ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ላይም ተጠናክሮ ከተሰራ  በዚህ አመት መጨረሻ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ይገኛል ብለዋል። ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ከቅርብ አመታት ወዲህ እያሽቆለቆለ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለዚህም ዘርፉ በአግባቡ አለመመራቱ በምክንያትነት የሚጠቀስ ሲሆን መንግስት እየወሰደ ባለው የአገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ላይ ትኩረት ከተሰጠው መስክ አንዱ የንግድ ስርአቱን ማሻሻል ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም