የመደመር እሳቤ አገራዊ እና ብሔራዊ ማንነትን ያስታረቀ መሆኑ ተገለፀ

1134
ጥቅምት 10/2012 የመደመር እሳቤ አገራዊ ማንነትን እና ብሔራዊ ማንነትን ያስታረቀ መሆኑን በአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ ሀሳባቸውን ያካፈሉ ባለሙያዎች ገለፁ። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው 'አዲስ ወግ' የውይይት መድረክ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፃፉት የመደመር መጽሐፍ ላይ ውይይት አካሂዷል። "መደመር" ለአገር በቀል ችግሮች "አገር በቀል መፍትሄ መሰጠት ይቻላል" የሚል ጽንስ ሀሳብ ይዞ መነሳቱ በመድረኩ ተገልጿል። በውይይቱ አገሪቷ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ያሉባትን ችግሮች በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደ መፍትሄ በቀረበው የ  "መደመር" አስተሳሰብ ላይ በስፋት በመወያየት መተንተን እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ተመርኩዞ የተካሄደው ይኸው ውይይት የመደመር መነሻ ሀሳቦች፣ የመደመር ፖለቲካዊ ገፅ፣ የመደመር እሳቤና ኢኮኖሚ ገጽ እንዲሁም መደመርና የውጪ ግንኙነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። መደመር በፖለቲካው ያለውን አንድምታ በተመለከተ ሀሳባቸውን ያካፈሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የወቅታዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍስሐ ይታገሱ "አብዮታዊ ዴሞክራሲ አገሪቷን ማሻገር አልቻለም" የሚለውን ጉዳይ አንስተዋል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሩሲያ ከፊውዳሊዝም ወደ ሶሻሊዝም ለመድረሰ ታስቦ የተሰራ ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን ሩሲያዊያን ብዙ ርቀት እንደማያስኬድ አምነው ማስተካከያ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ህብረተሰብን በመደብ የሚከፋፍል መሆኑን ጠቅሰውም ለአብነትም ትምክተኛ፣ ጠባብ፣ ተራማጅ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ልማታዊ እንዲሁም ጨቋኝ ተጨቋኝ እያለ የሚከፋፍል እንደሆነም አንስተዋል። ለኢኮኖሚ ቅቡልነት ብቻ ትኩረት የሚሰጠው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት ቦታ የማይሰጥ መሆኑን እና አገራዊ ማንነትና ብሄራዊ ማንነት ላይ የአስተሳሰብም ሆነ የአፈፃፀም ችግሮች ያሉበት መሆኑንም ዘርዝረዋል። በመጨረሻም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፓርቲና መንግስትን የሚቀላቅል መሆኑን አንስተው መደመር ግን የዚህ ተቃርኖ አስተሳሰብ ያለውም፤ ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታም ትኩረት የሚሰጥ እና ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለብኝ ብሎ የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ዮናስ ዘውዴ በመደመር መነሻ ሀሳቦች ዙሪያ ባቀረቡት ንግግርም፤ በርካታ የውጪ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶች አገሪቷን ይለውጣሉ ተብለው ቢተገበሩም "ሊያሻግሩ አልቻሉም" ብለዋል። "መደመር" ደመረ ከሚለው ግስ መውጣቱን ጠቅሰው ትርጓሜውም መሰብሰብ እና ማከማቸት በመሆኑ በተናጠል ከመፍጨርጨር ይልቅ ወደ አንድ መምጣትን ያመላክታልም ብለዋል። የተለያዩ እውቀቶችንና ሀብቶችን በአንድ ከሰበሰበ በኋላ ከተከማቸ እና ወደ ማካበት ደረጃ ካደገ የአገሪቷን የብልጽግና ጉዞ እንደሚያሳድገው ያላቸውን እምነት አካፍለዋል። የመደመር ሳንካዎች ናቸው ያሉቸውን ዋልታ ረገጥነት፣ አቅላይነት፣ እምቢተኝነት፣ ሙያ መናቅ፣ አድር ባይነት እና ህሊና ቢስነትን መታገል እንደሚገባም አሳስበዋል። የመደመርን ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ያነሱት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚና ፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረት ናቸው። እሳቸውም የመደመር የኢኮኖሚ እሳቤ ብልጽግናን ማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል። መደመር ብልጽግናን እውን ለማድረግ ነፃ ውድድር ላይ የተመሰረተ የገበያ ስርዓት መሆኑን እንደሚያምን አስረድተው፤ መደመር ጥራት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም ነው የገለፁት። የመደመርን የውጪ ግንኙነት እሳቤ ያብራሩት አቶ መሐመድ ራፊ በበኩላቸው የውጪ ግንኙነት መሠረቱ የሀገር የሕልውና ጥያቄ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በታሪኳ በቀጠና፣ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ  ስትጫወት የነበረውን ዐበይት ሚናና የዲፕሎማሲ ስኬት ውጤቶችን መደመር  ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል። መደመር ቀጠናዊ ትብብርን ያማከለ የኢኮኖሚ ትስስር እውን ለማድረግ እንደሚሰራ የጠቀሱት አቶ መሐመድ፤ መደመር ከውጪ ግንኙነት አንጻር ጎረቤት ሀገራትን በማስቀደም ብሔራዊ ክብርን የማስጠበቅ ዓላማ እንዳለውም ገልፀዋል መደመር ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን በማመቻቸትና አስጠብቆ ማቆየት፣ ያለፉ ስህተቶችን ማረምና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ማሟላት መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም