በሎሬት ፀጋዬ ስም ማዕከል ተሰየመ

109
አምቦ ጥቅምት 10 / 2012 በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ስም የተሰየመ የባህል ጥናትና ምርምር ማዕከል በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተከፈተ፡፡ ማዕከሉ በሥነ ጽሁፍ፣  በቲያትርና በአጠቃላይ በኪነ ጥበብ  ዘርፍ ባህልና ዘመናዊነትን መሠረት ያደረገ  ትምህርት የሚሰጥበት፣ምርምር የሚደረግበትና ዕውቀት የሚዳብርበት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ ማዕከሉን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ማዕከሉ ታላላቅ ምሁራንን ማፍራትው ዓላማው ያደረገ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ትላልቅ ሥራዎች  ያበረከቱትን ምሁራን ሥራዎች መርምሮና አውቆ  ክብር መስጠት ይገባዋል ብለዋል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ አምቦ ያበቀላቸው የሥነ ጽሁፍና ቲያትር ዘርፍ ምሁር እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንደነበሩም ተናግረዋል። በሥራዎቻቸው የተዛቡትን ታሪካዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች ሲተቹና እንዲስተካከሉ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ እንደኖሩም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ የአገሪቱን ታሪካዊና ማህበራዊ ግንኙነቶች ለማቃናት በብዕራቸው በመታተራቸው ለእስርና እንግልት መዳረጋቸውንና የአገሪቱን ብዝኃነትና የሕዝቦችን እኩልነት እንዳሳወቁ የተናገሩት ደግሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ናቸው፡፡ ታላላቆቻችንን የምናከብረው ታላቅ ሥራ ሰርተው ላለፉት ጀግኖቻችንን የሚያከብር ትውልድ ለመፍጠር መሆኑንም አመልክተዋል። አንጋፋውና ታዋቂው አርቲስት አበበ ባልቻ በበኩሉ ሎሬት ፀጋዬ  በሥራዎቻቸውም ደጋግመው አገራቸው ሲያነሱ እንደነበር አስታውሶ ፣ለሥራቸው ማዕከል መሰየም ስለማይበቃ ሐውልት ሊገነባላቸው ይገባል ብሏል፡፡ የመጫና ቱለማ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ደሪቢ ጉታ በበኩላቸው  ''ሎሬት ጸጋዬ አዋቂ ብቻ ሳይሆን ፤ ትምህርት ቤት ነበር'' ብለዋል፡፡ ታዋቂው ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ በ70 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በ1998 ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም