ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ደምቀዋል

59
ጥቅምት 10/2012 ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ትናንት በአውሮፓና በእስያ ከተሞች በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ደምቀው ታይተዋል። በሕንድ ኒው ዴልሂ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ሲያሸንፉ በሴቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል። አትሌት ፀሐይ ገመቹ 1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ስታሸንፍ፤ ባለፈው ዓመት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ራስ አል ካይማይ በርቀቱ ያስመዘገበችውን የግል ምርጥ ሠዓት በሰባት ሴኮንድ አሻሽላለች። ከውድድሩ በፊት የቦታውን ክብረ ወሰን የመስበር ዕቅዷ ባይሳካላትም በኢትዮጵያ በርቀቱ ስድስተኛ ፈጣን ሠዓት ማስመዘገቧን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዘገባ ያመለክታል። ፀሐይ ከሁለት ሳምንት በፊት በኳታር ዶሃ በተካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል። አትሌት ዓለምዘርፍ የኋላው 1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ1 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛ ስትወጣ አትሌት ዘይነባ ይመር በ1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች። አትሌት ዓለም ንጉስም ስድስተኛ ወጥታለች። በወንዶች ያለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ አትሌት አንድአምላክ በልሁ 59 ደቂቃ ከ10 ሴኮንድ አሸናፊ ሲሆን በርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓቱን በስምንት ሴኮንድ አሻሽሏል። በዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን የመጀመሪያ ውድድሩን ያካሄደው አትሌት ሰለሞን በሪሁ 59 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ ሁለተኛ ሲወጣ ኬንያዊው አትሌት ኪቢዮት ካንዴ 59 ደቂቃ ከ33 ሴኮንድ ሶስተኛ ሆኗል። ትናንት በተካሄደው የፖርቹጋል ሊዝበን ማራቶንም በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸንፈዋል። በወንዶች አትሌት አንዱዓለም ሽፈራው 2 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ በመግባት ሲያሸንፍ በርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓቱን ከሁለት ደቂቃ በላይ አሻሽሏል። ኬንያዊው አትሌት ሳሙኤል ዋንጂኩ በ2 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ1 ሴኮንድ ሁለተኛ፤ ሌላው ኬንያዊ ስቴፐን ቼምላኒ በ2 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ22 ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥተዋል። በሴቶች አትሌት ሰቻሌ ደላሳ 2 ሠዓት ከ29 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ በመግባት ስታሸንፍ ኬንያዊዋ ሄለን ጄፕኩርጋት 2 ሠዓት ከ29 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች። አትሌት ሱሌ ኡቱራ በ2 ሠዓት ከ32 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። በተያያዘ ትናንት በተካሄደው የሊዝበን ግማሽ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ኬንያዊያን አትሌቶች አሸንፈዋል። በሌላ በኩል ትናንት በኔዘርላንድ በተካሄደው የአምስተርዳም ማራቶን ደጊቱ አዝመራው በመጀመሪያ የዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሯ በ2 ሠዓት ከ19 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ አሸናፊ ሆናለች። እ.አ.አ በ2012 በኢትዮጵያዊቷ አትሌት መሰረት ኃይሉ ተይዞ የነበረውን የቦታውን ክብረ ወሰን በ1 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድም አሻሽላለች። አትሌት ትዕግስት ግርማ 2 ሠዓት ከ19 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ሁለተኛ ስትወጣ አትሌት አዝመራው ገብሩ 2 ሠዓት ከ20 ደቂቃ ከ48 ሴኮንድ በሶስተኝነት አጠናቃለች። ሁለተኛና ሶስተኛ የወጡት አትሌቶች በርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓታቸውን ያሻሻሉ ሲሆን የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን ያደረገችው አትሌት በሱ ሳዶ አራተኛ ወጥታለች። በወንዶች ኬንያዊው አትሌት ቪንሰንት ኪፕቹምባ 2 ሠዓት ከ5 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ አሸናፊ ሲሆን አትሌት ሰለሞን ደቅሲሳ 2 ሠዓት ከ5 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥቷል። ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ኤሊሻ ሮቲች 2ሰአት ከ5 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። በተጨማሪም ትናንት በካናዳ በተካሄደው የቶሮንቶ ወተር ፍሮንት ማራቶን በሴቶች ኬንያዊቷ ማግዴላይን ማሳይ 2 ሠዓት ከ22 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ አሸናፊ ስትሆን አትሌት ብሩክታዊት እሸቱ 2 ሠዓት ከ22 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች። ሌላዋ ኬንያዊት ቤትሲ ሳይና 2 ሠዓት ከ22 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ ገብታ ሶስተኛ ሆናለች። በውድድሩ አትሌት ብርቄ ደበሌ አራተኛ፣ አትሌት ሹኮ ገነሞ፣ አትሌት እታፈራሁ ተመስገንና አትሌት በቀለች ጉደታ በቅደም ተከተል ከሰባተኛ እስከ ዘጠነኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በወንዶች ኬንያዊው አትሌት ፒሊሞን ሮኖ በ2 ሠዓት ከ5 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ሲያሸንፍ አትሌት ለሚ ብርሃኑ 2 ሠዓት ከ5 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ በሆነ ውጤት ሁለተኛ ወጥቷል። ዩጋንዳዊው አትሌት ፌሊክስ ቼሞንጌስ 2 ሠዓት ከ5 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ በመግባት ሶስተኛ ሆኗል። የኒው ዴልሂ ግማሽ ማራቶን እንዲሁም የሊዝበን፣ የአምሰተርዳምና የቶሮንቶ ወተር ፍሮንት ማራቶን ውድድሮች በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጣቸው ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም