የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን የሚያስችል ሳይንሳዊ ጥናት ተጀመረ

122
ጥቅምት 10/2012 የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ይዘታቸውን እንደጠበቁ ለመጠገን የስነ-ምድርና የአርኪዮሎጂ ጥናት መጀመሩን የኢትዮ-ፈረንሳይ የጥናት ቡድን ገለጸ። የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ከፍተኛ የቅርስ ጥናትና ጥገና ባለሙያዎች በጋራ የተሳተፉበት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሙከራ ጥገና በመውጭው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ይጀምራል ተብሏል። በቁጥር 11 የሆኑት የቅዱስ ላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናት በ1970 ዓመተ ምህረት በዓለም አቀፍ የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት የዓለም ቅርስ ተብለው ተመዝግበዋል። በንጉስ ላሊበላ ዘመነ መንግስት በ12ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ይባስ ብሎ ከ10 ዓመት በፊት በአምስት ዓመት ጊዜ ይነሳል ተብሎ በ11 ሚሊዮን ዩሮ የተሰራው መጠለያ ተጨማሪ አደጋ በመሆን የቅርሱን ህልውና እየተፈታተነ ይገኛል። በመሆኑም በቅርሱ ላይ የደረሰውን የመሰንጠቅ አደጋ ለመጠገንና መጠለያውን ለማንሳት ዘርፈ ብዙ ሳይንሳዊ ጥናት እንደሚያስፈልግ አጥኝዎቹ ይናገራሉ። ቅርሱ ለተደቀነበት አደጋ መፍትሄ ለመፈለግ ከኢትዮጵያና ፈረንሳይ የተውጣቱ የቅርስ ጥናትና ጥገና ባለሙያዎች ከያዝነው የፈረንጆች ጥቅምት ወር ጀምሮ መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ። የፈረንሳይ የታሪካዊ ቅርሶች አርክቴክት ሃላፊና የኢትዮ- ፈረንሳይ ፕሮጀክት አስተባባሪ ረጊስ ማርቲን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በቅርሱ ላይ የተደቀነውን አደጋ በጥንቃቄ መመርመር ይገባል። የኢትዮጵያ መለያ የሆነውን አስደናቂ ቅርስ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ ለመጠገንና መጠለያውን በጥንቃቄ ለማንሳት በአርኪዮሎጂና አርኪዮቪዥዋል ጥናት መረጃ እየሰበሰብነ ነው ብለዋል። ስንጥቁን ለመጠገንና መጠለያውን ለማንሳት የአርኪዮሎጂ፣ የስነ ምድር፣ የቅርጽ ጥናት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በቅርሱ ላይ መረጃ ለመሰብሰብ የሚገጠሙ ስሪ ዲ ካሜራዎች በተጨማሪ በየሁለት ሰዓቱ መረጃ የሚያደርሱ በሌዘር ስካን መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለዋል። የአርኪዮሎጂ ዘርፍ ጥናት ቡድን መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሬ ላውሬ ደራት ከቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት መፈልፈል በፊት አሁን ባሉበት በቤተ ገብርኤልና ቤተ ጎለጎታ መካከል በ11ኛ መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ሰፊ የሰዎች መኖሪያ እንደነበር የሚያሳይ ቅሬተ አካል አግኝተናል ብለዋል። ቅሪተ አካል፣ ወፍጮ፣ አመድና ሆን ተብለው የተዘጋጁ ጥብር አለቶች መኖራቸው ደግሞ ከቅዱስ ላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ፍንጭ ይሰጣል ብለዋል። በመሆኑም ስለ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ በቂ መረጃና ይዘት ለማወቅ ከዚህ በላይ መስራት እንደሚገባንም ምልክት አግንተናል ነው ያሉት። በፈረንሳይ የጥናት ፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወይዘሮ ፌቨን ተወልደ ከተለያዩ ጥናቶች የተሰበሰቡ መረጃዎች በየስድስት ወሩ ትንተና ይደረግባቸዋል ብለዋል። እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ህዳር 2020 የትንተና ውጤቱ ቀርቦ በመንግስት ይሁንታ ሲያገኝ ጥገናው እንደሚጀመር ገልጸዋል። ይሁን እንጂ  የጉዳት መጠናቸው ጊዜ የማይሰጥ ቅርሶች እየታዩ ጥገና ይደረጋል፤ በመውጭ የፈረንጆች አዲስ ዓመት ቤተ-ጎለጎታ የሙከራ መጠለያ ይሰራለታል ብለዋል። የሚሰሩ መጠለያዎች ቢወድቁ በቅርሱ ላይ ምንም አይነት ጉዳት የማያደርሱና የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ እንዲገልጹ ተደርገው ከእንጨት የሚዘጋጁ መሰሶዎች እንደሚሆኑም ገልጸዋል። በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የአለም ዓቀፍ ቅርሶች አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሀይ እሸቴ ቅርሱ በዩኔስኮ የቅርስ አስተዳደርና እድሳት ህግ መሰረት መጠገን የሚያስችል የባለሙያዎች ስብስብ ይዟል ብለዋል። የቅዱስ ላሊበላ አብያተ-ክርስቲያናት የዓለም ቅርስ በመሆናቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥናቱ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ጥገናው እንደሚከናወን ገልጸዋል። የቅዱስ ላሊበላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ወልደሚካኤል የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኅብረተሰቡ የማንነት መገለጫዎች በመሆናቸው ቶሎ መጠገን ይኖርባቸዋል ይላሉ። የቅርስ ጥገና ጥንቃቄ ስለሚፈልግ ኅብረተሰቡ ቶሎ መጠገን አለባቸው የሚለው ፍላጎትና ሳይንሳዊ ጥናቱ የሚወስደው ጊዜ ተጣጥሞ መሄድ ይኖርበታል ብለዋል። በተለይም የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በባህርያቸው ውስብስብ በመሆናቸው ሳይንሱ በሚጠይቀው የጊዜ ፍጥነት መከናወን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም