ኢትዮጵያ ሴቶችን ለማብቃት የምታከናውነውን ተግባር እንደሚደግፍ ተመድ አስታወቀ

81
ጥቅምት 10/2012 ኢትዮጵያ ሴቶችን በከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ በማብቃት ረገድ የምታከናውነውን ተግባር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እንደሚደግፍ አስታወቀ። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ሁለቱ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ በቀጣናው በምታከናውናቸው ተግባራት ላይ ሰፊ ምክክር አካሂደዋል። ኢትዮጵያ ሴቶችን በከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ በማብቃት ረገድ የምታከናውነውን ተግባር በታችኛው የአስተዳደር እርከን ላይ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል። በተለይ በታችኛው የአስተዳደር እርከን ላይ ሴቶችን ለማብቃት ኢትዮጵያ የምታከናውነውን ተግባር ተመድ እንደሚደግፍ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያደረገችው የሰላም ስምምነት ጥቅሙ ለሁለቱ አገሮች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው መረጋጋት አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። የተመድ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ከአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ጋር እንደሚሰራ ምክትል ዋና ፀሐፊዋ አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያገኙት የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት የአፍሪካም ጭምር መሆኑን ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላም ዙሪያ በምታከናውናቸው ተግባራት ዙሪያ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ባከናወኗቸው ተግባራት ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል። በቀጣናው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ተገቢውን ሚና መጫወቷን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብርሃም ግርማይ ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል። ለአንድ ሳምንት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በኢትዮጵያ የጀመሩት የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ በኤርትራ፣ በጂቡቲና በሶማሊያ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም