ውህደቱ የብሄር ብሄረሰቦችን አንድነት ያጠናክራል - ምሁራን

54
ጥቅምት 10/2012 የፖርቲዎች ውህደት ኢትዮጰያ አሁን ካለችበት ውስብስብ ችግር በማውጣት አንድነቷንና ሰላሟን ጠብቃ እንድትቀጥል የሚያደርግ መሆኑን ምሁራን ገለፁ። በአተገባበሩ ዙሪያ ተገቢውን ውይይትና መግባባት በመፍጠት በጥንቃቄ ሊከናወን እንደሚገባውም አሳስበዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደዉ 5ኛዉ አገር አቀፍ የባህልና ኪነ ጥበብ አዉደ ጥናት የተሳተፉት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የቋንቋና ስነ-ጹህፍ መምህርና የግጭት አፈታት ተመራማሪ ዶክተር ገብረየሱስ ተክሉ ለኢዜአ እንደገለፁት ውህደቱ ለኢትዮጰያ አንድነት ወሳኝ ነው። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚከሰተውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል ውህደቱ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ታዳጊ ክልሎችም በአዲስ መንፈስ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም አሁን እየተስተዋለ ያለውን መተቻቸት፣ መናናቅና የጸጥታ ችግር ለመፍታት ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ እንደ ዶክተር ገብረየሱስ ገለጻ አተገባበሩ ግን አሁን ባለበት የፖለቲካ ፍጥጫ ሳይሆን ጊዜ ተሰጥቶት በየደረጃው ዉይይትና መተማመን ተፈጥሮበት ሊተገበር ይገባል፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ሀይሉ በበኩላቸዉ ውህደቱ አግላይነትን ከመቅረፍ ባለፈ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሰላምና የመቻቻል እሴት ያጎለብታል፡፡ በህዝብ ተጋድሎ የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስም የውህደቱን አላማና ጥቅም በማስረዳትና ህብረተሰቡን በማወያየት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በአንድ ላይ በሚኖሩባት አገር ውህደቱ ጨፍላቂና አሃዳዊ ነው የሚባለው ግን መሰረተ ቢስ እና ፖለቲካዊ ይዘት የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ''አተገባበሩ ግን ጥንቃቄ ይፈልጋል'' ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ከዚህ በፊት የነበረው ፖለቲካ አግላይ፣ የበላይና የበታች የነበረበት እንደሆነም አብራርተዋል። እህትም ሆኑ አጋር ድርጅቶች  እርስ በእርስ ከመጠላላት ተቆጥበዉ እንደ አገር አንድ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡ ''የፖለቲካ ጥቅመኞች ህብረተሰቡን በብሄርና በሐይማኖት ከፋፍለዉ አገርን በማተራመስ የግል ጥቅማቸዉን ለማካበት በሚሮጡበት በዚህ ወቅት ውህደቱ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው'' ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነጹህፍ መምህርና የታሪክ ተመራማሪዉ ዶክተር ተሾመ መንገሻ ናቸዉ፡፡ ዉህደቱ አገራዊ መግባባትን የሚፈጥር፣ ችግሮችን የሚቀርፍ አዲስ የፖለቲካ ህዳሴ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም