በአፋር ከ26 ሺህ በላይ ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው

70
ሰመራ ጥቅምት 10/ 2012 በአፋር ክልል ከ26 ሺህ በላይ ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ዛሬ መሰጠት ተጀመረ። የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ ለአምስት ቀናት በሚካሄደው የክትባት መርሐ ግብር 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች ይሰጣል። ክትባቱ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በመንግሥት ጤና ተቋማትና ለክትባቱ በተዘጋጁ አማካይ ቦታዎች እንደሚሰጥም ተናግረዋል። ክትባቱ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያመጣ ያስረዱት ኃላፊው፣ኅብረተሰቡን ለማስተማር ከማህበረሰብ መሪዎች ጋር አስተምህሮ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልከተዋል። በሽታውን ለመከላከል የሚቻለው አንዲት ልጃገረድ በሁለት ዙሮች የሚሰጠውን ክትባት በአግባቡ ስትወስድ እንደሆነ አብራርተዋል። በዚህም የመጀመሪያው ዙር ክትባት የሚወስዱ ልጃገረዶች ሁለተኛውን ዙር ክትባት ከሰድስት ወር በኋላ  መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። በሰመራ ከተማ የሚግሌኪቦ ትምህርት ቤት ተማሪ ሐሊማ ሙሳ ክትባቱን ለሁለተኛ ጊዜ የወሰደችው ከበሽታው ራሷን ለመጠበቅ እንደሆነ ገልጻለች። በክልሉ ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው መርሐ ግብር 9ሺ 605 ልጃገረዶች  ክትባቱን ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚወስዱ አስረድተዋል። የማህፀን ካንሰር በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ .በሽታው በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ይከሰታል።በተለይ በ40ዎቹና በ50ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን ሴቶች እንደሚያጠቃ  መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም