የቡኖ በደሌ ዞን ነዋሪዎች የመሰረተ ልማት ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የቡኖ በደሌ ዞን ነዋሪዎች የመሰረተ ልማት ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ
መቱ፤ ኢዜአ፤ ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓም በኦሮሚያ ክልል የቡኖ በደሌ ዞን ነዋሪዎች በአካባቢያቸውን የሚታየውን የመሰረተ ልማት ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ ።
የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ መንግስት የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በልማት በኩል ያሉባቸውን ችግሮች በመገንዘብ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል ::
የቡኖ በደሌ ወረዳ ነዋሪዎች የልማት ጥያቄአቸውን ያቀረቡት ትናንት ከክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው ።
ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የክልሉ መንግስት ያሉባቸውን የልማት ችግሮች እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል::
በውይይቱ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል መንግስት በየጊዜው የሚቆራረጠው የመብራት አገልግሎት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ በአፋጣኝ ሊፈታልን ይገባል ብለዋል ።
የበደሌ ሆስፒታል ለአካባቢው ማህበረሰብ የተሟላ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ወደ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲያድግላቸውም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል ።
የመቱ ዩኒቨርስቲ የበደሌ ግብርናና ደን ሳይንስ ኮሌጅ ወደ ሙሉ ዩኒቨርስቲነት እንዲያድግላቸውም ነዋሪዎቹ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ አንስተውላቸዋል ::
በአካባቢው ለቡና ፣ አትክልትና ፍራፍሬና ለማር ምርት ያለውን አመቺነት በመጠቀም አርሶአደሩ ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል::
ወደ ዴዴሳ ወረዳ በሰፈራ መልክ የመጡና በቂ መሬት ያላገኙትን አባወሯዎች ችግር ለመፍታትም የክልሉ መንግስት እየሰራ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ እንደሚቀረፍ አስረድተዋል::
መንግስት የልማት ችግሮችን ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል ::