የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እውቅና ሰጠ

63
መቐለ ኢዜአ ጥቅምት 10/12 ዓ/ም የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የክልሉን ባህል፣ቋንቋ፣ታሪክና ማንነት በማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋፀኦ አበርክተዋል ላላቸው ሶስት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ትናንት የገንዘብ ሽልማትና እውቅና ሰጠ። እውቅና የተሰጣቸው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የትግራይ ህዝብ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላትና ታሪካዊ ስፍራዎችን በተለያዩ ሚድያዎች በማስተዋወቅ የላቀ ድርሻ የተወጡ መሆናቸውን ቢሮው ገልጿል። እንዲሁም የህዝቡ ባህልና ወግ፤ፍቅርና አንድነት የሚገልፁ ባህላዊና ዘመናዊ ዘፈኖችን በማቅረብ አርአያነታቸውን የተወጡ ሲሆን ለእያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር ሽልማትና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶአቸዋል። በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አማካኝነት ትናንት ማምሻውን በዓዲግራት ከተማ በተዘጋጀው የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ እውቅና የተሰጣቸው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋዜጠኛና ደራሲ ደስታ ካህሳይ፤በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ህመም ምክንያት የአልጋ ቁራኛ የሆነችው ዝነኛዋ የትግርኛ ዘፋኝ ንግስቲ ሐየሎምና የኪነ ጥበብ ባለሙያ የሆነው ታደሰ ደስታ ናቸው። ሽልማቱን የሰጡት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ብርክቲ ገብረመድህን ባሰሙት ንግግር ‘’ሽልማታችን ከገንዘብ በዘለለ የታሪካችንና የቅርሳችን አካል ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ ታላቅ ክብር የሚሰጠው ነው ብለዋል ’’ ሁላችንም የየአካባቢያችን ታሪክ ፤ባህልና ቋንቋ በመጠበቅና በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ልንጫወት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል ። በሶስት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተጀመረው የማበረታቻ ሽልማት ለወደፊቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ወይዘሮ ብርክቲ ተናግረዋል ። ከተሸላሚ የጥበብ ባለሙያዎች መካከል የድምፅ ወያነ ጋዜጣኛና ደራሲ ደስታ ካህሳይ እንዳለው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በዘርፉ የጀመረው የእውቅና መስጠት ስነ ስርዓት በጣም መልካምና አስደሳች መሆኑን ገልጿል። በክልሉ ታሪክ፣ባህልና ቋንቋ ያተኮረ መፅሃፍ አሳትሞ ለአንባቢያን ለማቅረብም እቅድ እንዳለው ደራሲው በዚህ ወቅት ተናግሯል። በባህላዊ ዘፈን የሚታወቀው የኪነ ጥበብ ባለሙያ ታደሰ ደስታ በበኩሉ ከኛ የበለጠ ለክልሉ አስተዋፀኦ ያበረከቱ ሙያተኞች ስላሉ ሽልማቱ የእነሱም ጭምር በመሆኑ በጋራ ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳ ነው ብሏል ። በመድረኩ ላይ የተገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም እንደዚህ ዓይነት የማበረታቻ ሽልማት በብዛትና በስፋት የሚያሳትፍ ሆኖ በየዓመቱ እንዲቀጥል አስተያየታቸውን ሰጥቷል። በእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ ከግልና ከመንግስት ተቋማት የተወከሉ ከ300 በላይ ምሁራን፤የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችናና  ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም