የሃዋሳን ከተማ ሰላም ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው

44
ጥቅምት 9/2012 የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ሠላማዊ እንቅስቃሴ ለማስቀጠልና የነዋሪዎችን አብሮነት ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በወቅታዊ ጉዳዮችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በከተማዋ ከሚገኙ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ እህት ድርጅቶች አባላት ጋር ተወያይተዋል ፡፡ አቶ ጥራቱ በየነ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በከተማዋ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተፈጥረው የነበሩ የፀጥታ ችግር ነዋሪዎች በሥጋት እንዲኖሩ እያደረጉት ነው፡፡ ''የፀጥታው ችግር ሁላችንንም ጎድቶናል'' ያሉት አቶ ጥራቱ በዕለት ገቢ ከሚተዳደሩት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ባለሀብቶች የፀጥታው ችግር አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳረፈባቸው አስረድተዋል ፡፡ አሁን ላይ ሀዋሳ ቀድሞ ወደ ምትታወቅበት ሠላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰች ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው ደግሞ የፀጥታ አካላት ብቻ ሳይሆን ሰላም ወዳድ የሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች ጥረት ጭምር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች አብሮነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ ይህንን እንቅስቃሴ ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ አስተዳደሩ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ከነዋሪው ጋር ምክክር በማድረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በእለቱ በከተማዋ ከሚገኙ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ እህት ድርጅቶች አባላት ጋር የተካሄደው ውይይትም የዚሁ አካል መሆኑንና የተጀመረውን ሰላም የማስጠበቅ ሥራ ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ህዳር 10 የሚደረገው የሲዳማ በክልል የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና ሁሉም የራሱን ኃላፊነት እንዲወጣ ከነዋሪዎች ጋር የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሆነ አስረድተዋል ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ የገለፁት አቶ ጥራቱ ከተማዋ ከዚህ በፊት ወደ ነበረችበት የፀጥታ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንድትመለስ ፤ አሁን የተገኘውን ሠላምም አጠናክሮ ለማስቀጠል የፖሊስ መዋቅሩን የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ እንደሆነም አብራርተዋል ፡፡ በዚህም መካከለኛና ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች የአመራር ክህሎታቸውን የሚያጎለብቱበትን የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ገልፀዋል ፡፡ በቀጣይ ዙሮችም ተመሳሳይ ሥልጠናዎች ለሁሉም የፀጥታ አካላት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል አቶ በለጠ ከተማ ''ሠላምን የማስጠበቅ ስራ የተወሰኑ አካላት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ኃላፊነት ነው'' ብለዋል ፡፡ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን ቅሬታዎች ለማዳመጥና ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚበረታታ እንደሆነ ገልፀው ''በእኛ በኩል የእርስ በዕርስ ትሥሥራችን የማጠናከርና ሠላማችንን የመጠበቅ ኃላፊነታችንን እንወጣለን'' ብለዋል ፡፡ አቶ ደሳለኝ ታደለ በበኩላቸው ''ሠላምን የማስጠበቅ ስራ ከእንዳንዳችን ቤት ይጀምራል'' ብለዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን አዋዋላቸውን መከታተልና አመለካከታቸውን እንዲያስተካከሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል ፡፡ አሁን ያለው የከተማዋ ሠላም እንዲቀጥልና በመጪው ህዳር ወር የሚደረገው ህዝበ ውሳኔ ያለሥጋት እንዲካሄድ ከአመራር አካላት ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ ተናግረዋል ፡፡ ''ተቀራርበን ከተወያየን የማንፈታው ችግር የለም'' ያሉት አቶ ክፈተው አየለ ደግሞ እኔ ያልኩት ብቻ ከሚል አመለካከት መውጣትና ሁሉንም በሚጠቅም ሀሳብ ላይ መስማማት ተገቢ እንደሆነ አመልክተዋል ፡፡ ''ሀዋሳን ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀደመ ገፅታዋ ለመመለስና እንደ ሀገርም የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ የሰመረ ለማድረግ ሁላችንም የድርሻችንን ማበርከት ይገባናልም'' ብለዋል ፡፡ በዚህ ረገድ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም