በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ባለመኖሩ ተቸግረናል - የደብረ ብርሃን ከተማ ወጣቶች

49
ደብረ በርሃን ሚያዝያ 28/2010 በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ባለመኖሩ መቸገራቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ወጣቶች ገለፁ። ችግሩን ለመፍታት 15 መለስተኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡ በደብረብርሃን ከተማ የ04 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ይበልጣል እሸቱ ለኢዜአ እንደገለፀው በከተማዋ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ባለመኖሩ በተለያዩ ስፖርቶች ራሱን አብቅቶ ተወዳዳሪ ለመሆን ያለውን አላማ ለማሳካት እንቅፋት ፈጥሮበታል፡፡ በተለይ የእግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት እንዳለው የገለፀው ወጣቱ ይህንን ፍላጎቱን ለማሟላት በእረፍት ጊዜው ከአቻዎቹ ጋር ለመለማመድ  እንዳልቻለ ገልጿል፡፡ የ08 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አሰፋ አበበ በበኩሉ በመጫዎቻ ሜዳ ችግር እሱን ጨምሮ አብዛኛው የከተማው ወጣት ተመልካች ከመሆን የዘለለ ተሳታፎ እንደሌላቸው ተናግሯል። በዚህም ምክንያት የእረፍት ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ለመዋል እየተገደዱ መሆኑን ገልጿል፡፡ በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የባህል ቱሪዝም፣ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ማሞ በሰጡት ምላሽ የወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር እየተሰራ ነው፡፡ ቀደም ሲል የስፖርት ማዘውተሪያና መዝናኛ ቦታዎችን ለማስፋፋት የቦታ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን ከየቀበሌው አስተዳደር ጋር በተደረገ ውይይት  ለስፖርት ማዘውተሪያ የሚሆን ቦታ ዘንድሮ በመፈቀዱ የ15 መለስተኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ግንባታ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ በተለያዩ ቀበሌዎች በሚገኝ 1 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ በ3 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታው በመካሄድ ላይ ያለው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የእግር፣ መረብ፣ ቅርጫትና እጅ ኳስን ጨምሮ የአትሌቲክስ መሮጫን ያካተተ ነው፡፡ በጅምር ላይ ያሉ ማዘውተሪያ ቦታዎች ሲጠናቀቁ በከተማው ያሉ ከ27 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም