ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተበረከተው የኖቤል የሰላም ሽልማት የአፍሪካን ተረክ የቀየረ ነው

91
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 8/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተሸለሙት የኖቤል የሰላም ሽልማት አፍሪካን በተመለከተ የሚነገሩ ተረኮችን የቀየረ መሆኑን በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ አለም ተናግረዋል። አምባሳደሩ ከኬኒያው ኔሽን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ''ሽልማቱ ኢትዮጵያን፣ የአፍሪካ ቀንድንና አህጉሩን አወንታዊ ገጽታ ያላበሰ ነው'' ብለዋል። ኢትዮጵያ በሽልማቱ በመታገዝ የኢንቨስትመንትና የንግድ መዳረሻ ለመሆን የያዘችውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነም ገልጸዋል። አዲሲቷ የተስፋ ምድር የተባለችው ኢትዮጵያ ባለፉት 15 አመታት በተከታታይ ባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገቧንም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚዋ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ለመሆን እየሰራች መሆኑንም በመጥቀስ። አምባሳደሩ እንደተናገሩት፤ በአፍሪካ ቀንድ ከሚኖረው ህዝብ ግማሽ የሚጠጋውን የያዘችው ኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ፣ ወጣት ትውልድና የሰለጠነ ባለሙያ አፍርታለች። የአገሪቱ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በአፍሪካ ቀንድ የሰፈነው ሰላም ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዳደረጋትም ጠቁመዋል። ''አገሪቱ ያላት ያልተነካ የተፈጥሮ ሃብት፣ በዝቅተኛ ዋጋ የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ሃይልና የተረጋጋ ሰላም መጨበጧ ተመራጭ ያደርጋታል'' ብለዋል። በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከአለም አገሮች ከፍተኛ ሰራዊት በማዋጣት ግንባር ቀደም መሆኗንም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ መሪዎች በአፍሪካ ሰላም እንዲሰፈን የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። የሱዳን ችግር በአፍሪካ ህብረትና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥረት መፈታቱን ተናግረው፤ ''ኢትዮጵያ በአፍሪካና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት አገሮች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች'' ብለዋል። አገሪቱ ሰላምን ለማስፈን እያደረገች ያለው ጥረት ከአፍሪካ ውጭ ካሉ አገሮችም ሰላም እንዲወርድ እንድትሰራ ጥሪ እንዲቀርብላት አድርጓታል በማለት የሽልማቱን ጠቃሚነት አሳይተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም