የ“መደመር “ መጽሐፍ የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንደተጠበቁ የሚያስቀጥል እሳቤዎችን ያካተተ ነው---አቶ ሙስተፌ ሙሁመድ

74
ጥቅምት 8/2012 የ“መደመር “ መጽሐፍ ብሔሮች ፣ ብሔሰቦችና ህዝቦች ያገኟቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንደተጠበቁ የሚያስቀጥል እሳቤዎችን ያካተተ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተደድር አቶ ሙስተፌ ሙሁመድ ገለጹ። ርዕሰ መስተዳድሩ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች ተወካዮች ጋር በመሆን “መደመር” መጽሐፍን ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ መርቀዋል። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ወቅት  አቶ ሙስጠፌ በመጽሐፉ ይዘት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። መጽሐፉ የሰዎችን ባህሪ በማመላከትና ሀሳብን ይዞ በመውጣት የተለየ እንደሚያደርገው አስረድተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በማብራሪያቸው የመጽሐፉ እይታዎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እስካሁን ያገኟቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንደተጠበቁ የሚያስቀጥል እሳቤዎችን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል። በምረቃው ሰነሰርዓት ከተገኙት ነዋሪዎች መካከል ሼክ አደን መሐመድ በሰጡት አስተያየት “በመፅሐፉ የተነሱ ሀሳቦች የክልሉን ህዝብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካ ጥያዎችን ለመመለስ የሚያግዙ ናቸው” ብለዋል ። አቶ አብዲራህማን ኢድ በበኩላቸው መጽሐፉ የተመዘገቡ የምጣኔ ሀብት ስኬቶችን ከወቅቱ ጋር በማስቀጠል  በየአከባቢው ያሉት የተፈጥሮ ሀብቶችን እንዲለሙ የሚያደርግ እይታዎች እንደያዘ መመልከታቸውን ተናግረዋል። በመጽሐፉ ምረቃ ስነስርዓት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ መሀመድ ሰኢድ ፣ የክልሉ መንግስት ስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል። በአማርኛ፣ ኦሮሚኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተፃፈ “መደመር “ መጽሐፍ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለትምህርት ልማት የሚውል እንደሆነ ተመልክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም