መደመር መልካሙ ጎኖችን አጠናክረንና ስህተቶቻችንን አርመን አብረን የምንዘልቅበት ነው---ሚኒስትሯ ወይዘሮ ኤይሻ መሃመድ

57
ሰመራ/ ሚዛን ኢዜአ ጥቅምት 8/2012፡- “መደመር የነበሩንን መልካም ጎኖች አጠናክረንና ስህተቶቻችንን አርመን አብረን የምንዘልቅበት ነው “ ሲሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ወይዘሮ ኤይሻ መሃመድ ገለጹ። የዶክተር አብይ አህመድ “ መደመር” መጽሐፍ በአፋር ክልል ደረጃ ዛሬ በሰመራ የተመረቀ ሲሆን በተመሳሳይ በሚዛን አማን ከተማም ስነስርዓቱ ተከናውኗል። በሰመራው ስነ-ስርዓት የተገኙት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ኤይሻ መሃመድ በመደመር ፍልስፍናና በመጽሐፉ ዙሪያ ለተሳተፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህ ወቅት “መደመር መጽሐፍ ትናንት የነበሩንን መልካም ጎኖች አጠናክረንና ስህተቶቻችንን አርመን አብረን የምንዘልቅበት ሁኔታ የሚያስቀምጥ ነው “ ብለዋል። መጽሐፉ የአመለካከት ብዝሃነትን አክብሮ በጋራ እንደ ሀገርና ህዝብ አብሮ የሚያስቀጥሉ እሴቶችን በማጎልበት አንድነትን ጠብቆ መዝለቅ እንደሚቻል ያሳያል። “በአጠቃላይ በሀገራችን የፖለቲካ ሂደት ከመጠላለፍና ሴራ ፖለቲካዊ እሳቢ ወጥተን በግልጽ በመወያየትና በመደጋገፍ ችግሮቻችንን እየፈታን በጋራ የምንሄድበት ባህልን የሚስተዋውቅ ነው “ ሲሉም ተናግረዋል። በህዝቦች ጠንካራ ትግል የመጣውን ለውጥ  ሀገራዊ አንድነት ጠብቆ ለማስቀጠልና ለማጠናከር  ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣም ሚኒስትሯ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የመጽሐፉ መመረቅ በሀገራዊ የፖለቲካ ሂደት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እስከ ህብረተሰቡ ድረስ ወጥ የሆነ ግንዛቤ ይዘው ለውጡን በብቃት ለማሳካት የጎላ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። ስለ ፌዴራሊዝም፣ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትና ተያያዥ ሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በተለያዩ ወገኖች የሚነሱ የተሳሳቱ ሃሳቦችን የሚጠራ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ ባለፈ ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለትምህርት ልማት የሚውል በመሆኑ ሁሉም በመግዛት የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። በምረቃ ስነ-ስርዓት ወቅት የተገኙት የሰመራ ከተማ ነዋሪ ሼክ መሀመድ አህመድ በሰጡት አስተያየት መደመር አንድነት እንዲጠናከር በማበረታታት ተቀባይነት ያለው ጠቃሚ ሀሳብ እንደያዘ መመልከታቸውን ተናግረዋል። ወጣት ኡመር ሙሳ “መጽሐፉ ሁሉም የራሱን ማንነትና እሴቶች ይዞ በመጻኢ የጋራ እድሎቻችን አብረንን የምንወስንበትን ሁኔታዎች የሚያሳይ ነው “ ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለባቸውን ከባድ የስራ ጫና ተቋቁመው መጽሐፉን በማበርከታቸው አድናቆቱን ገልጾ ይህም ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ ከሰራ ለውጥ ማምጣት እንደሚችም የሚያስተምር ሆኖ እንዳገኘው ተናግሯል። የክልሉና የፌደሬል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በምረቃው ስነሰርዓት ተገኝተዋል። በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  “መደመር" መጽሐፍ በሚዛን አማን ከተማ ዛሬ ሲመረቅ የደቡብ ክልል ፣የቤንች ሸኮ ምዕራብ ኦሞና ሸካ ዞኖች አመራሮችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የስነስርዓቱ ተካፋይ ነበሩ ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም