'ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ' በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸናፊ የሆነበትን ሽልማት ተቀበለ

119
ጥቅምት 8/2012 'ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ' እያከናወናቸው ባሉት ሰፋፊ ስፖርታዊ ኩነቶች ባስመዘገበው ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸናፊ የሆነበትን ሽልማት ትናንት ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓም በብሪታኒያ ሎንደን በተከናወነ ስነ-ስርዓት ተቀበለ። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 'ቻለንጅ አዋርድ' በሚለውና ደማቅና የተሳኩ ውድድሮችን ለሚያዘጋጁ አካላት የሚሰጠውን ሽልማት ነው ያገኘው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማዘጋጀት ከዓለም ቀዳሚ ተብሎ እውቅና የተሰጠው ባለፈው ወር ነው። ይህም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የአገሪቱን ስም በበጎ መልኩ ከማስተዋወቅ ባሻገር ትልቅ ብሔራዊ ሀብትም ጭምር መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታቋል። ለዚህ ስኬት እውን መሆን በተለያየ መንገድ ሰዎች ድምጽ እንዲሰጡ የጋበዙ፤ ጥሪ ያቀረቡና ያመቻቹ አካላትን እንዲሁም በድሉ የተደሰቱትን አመስግኗል። ከ18 ዓመት በፊት በ10 ኪሎ ሜትር፤ 10 ሺህ ስዎችን በማሳተፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር የጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተወዳዳሪው ቁጥር ከ45 ሺህ ልቋል። በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ እውቅናና ተሳትፎ ያላቸውን የጎዳና ውድድሮች አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚያሰናዳውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመሰረተው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ነው። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ለ19ኛ ጊዜ በመጪው ህዳር ወር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም