የእናት መቀነት…

99
ደሞዝ አያሌው /ኢዜአ/ በእግራቸው ስር ከሚገኝ ምድራቸው ፈልቆ በከንቱ ሲፈስ ፣ለዘመናት በድህነት ሲማቅቁ ለኖሩት ኢትዮጵያውያን ይህ ነው የሚባል የሚጠቀስ ፋይዳ ሳይሰጥ እንዲሁ በመንገዱ ላይ ያገኘውን ግሳንግስና ለም አፈር ጭምር በሙሉ ጠራርጎ በመውሰድ  ከመወለድ ውጭ የእናትነት ውለታውን ከፍሎ አያውቅም። አሁን ግን ህዝቦቿ ለዘመናት በወንዙ ያለመጠቀም ቁጭትን ምላሽ ለሰጠው የህዳሴ ግድብ የአንችልም አስተሳሰብን በመስበርና ታላቅ አገራዊ መግባባት በመፍጠር አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ግንባታው ለአፍታም ሳይቋረጥ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ መጋቢት 24 2003 ዓ/ም ሲቀመጥ ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በንግግራቸው "የዘመናት የልማት ህልማችንን እውን ለማድረግ፣ መላው የሃገራችን አርሶአደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዘመቻ እንደሚሳተፉ እምነቴ የፀና ነው" ነበር ያሉት፡፡ "በሀገር ውስጥ ብሎም በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሚያደርጉት ሁለንተናዊ  ርብርብ በመገንባት ለሀገር ተረካቢው ትውልድ ከድህንት የተላቀቀች ሀገር ለማስተላለፍ የሚገነባ የአቅመቢስነትን ታሪክ የሰበረ ሀውልት ነው" በመላትም ገልጸውታል፡፡ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን የምታለማው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ እንጂ ማንንም በሚጎዳ መልኩ እንዳልሆነ በበርካታ ብዙሃን መገናኛዎች በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በርካታ የውይይት መድረኮችን ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በከፍተኛ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በማድረግ የሚፈጠሩ ጥርጣሪዎችንና አለመግባቶችን በመፍታትም ነው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ያገባደደችው፡፡ይህ የሕዝብ ትብብርና ድጋፍ የፕሮጀክቱ የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ዓመት ተግባራዊ መደረግ ተጀምሮ አፈጻጸሙ አሁን ላይ ከ65 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብትን ወደ ተግባር ስትለውጥ በራስ አቅም በርካታ ጥናቶችን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በኢትዮጵያና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ስምምነት መሰረት የአለም አቀፉ የጥናት ቡድን በማዋቀር ተጨማሪ ጥናቶችን እንዲያካሂድና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች ላይ የሚያደርሰው ተጸእኖ አነስተኛ መሆኑን እንዲረጋገጥ በማድረግ ጭምርም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የፍትሀዊ ተጠቃሚነት መብትን ለማረጋገጥ ባከናወነቻቸው ስራዎችም ውጤት መመዝገቡን ነው ምሁራን  በአስተያየታቸው የገለጹት ፡፡ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር  ተስፋዬ ተሾመ  ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባት ሂደት ያስኘችው ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ጥቅሞች በርካታ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ድንብር ታሻጋሪ ወንዞችን በጋራ ማልማትና በፍትሀዊነት መጠቀም የክፍለዘመኑ የሰለጠነ  አካሄድ  መሆኑን የገለጹት  ረዳት ፕሮፌሰሩ፤  ድንበር ተሻጋሪ  የሆነው የአባይ ወንዝ 11 ሀገራትን የሚያጋራ ቢሆንም  ከተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ  አንዷ የሆነችው ግብጽ ዘመን ካለፈበት ለብቻዬ  ልጠቀም   አስተሳሰብ ላለመውጣትና ሌሎቹን ሀገራት የበይ ተመልካች  የሚደረገውን ሂደት ለማስቀጥል ያላትን ፍላጎት አሁንም ስታንጸባርቅ  ይታያል ፡፡ "ግብጾች አባይ የኛ ነው ይላሉ ነግር ግን የወንዙ ዋነኛ አመንጭ  ሀገር  ለብቻየ ልጠቀም የሚል አስተሳሰብ  የላትም "ያሉት ዳይሬክተሩ ፤የዘመኑ አስተሳሰብ የሆነውን  የጋራ ሀብትን በጋራ አልምቶ የመጠቀም  መርህን የተከትል  አለማቀፍ ተቀባይንት ያለው አካሄድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ አባይን በጋራ አልምቶ በፍትሃዊነት መጠቀም ይገባል የሚለውን አስተሳሰብ በተፋሰሱ ሀገርት ውስጥ እንዲሰርጽ በሰራችው ግንባር ቀደም የዲፕሎማሲ ስራም  አብዛኞቹ   የተፋሰሱ ሀገራት  እንዲደግፉት ፣በወንዙ የተወሰነ ተጠቃሚ የሆነችው ሱዳን  ጭመር ድጋፉን እንድትቀበለው በማድርግ በቀጠናው ጂኦፖለቲካል አስተሳሰብ ላይ  ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ ያስቻለ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ አብራርተዋል፡፡ " ኢትዮጵያ ከጅምሩ አባይ የግጭት መንስኤ አይደልም፤ የጋራ የሆነውን  ወንዝ በጋራ አልምተን ፍትሃዊ በሆነ ምልኩ የምንጠቀምበት እንጂ" የሚለውን አቋም በግልጽ  በማሳወቅና የፕሮጀክቱን ግንባታ ጭምር አለምአቀፍ ተቋማትና የተፋሰሱ  ሀገራት እንዲጎበኙ መፍቀዷ ትልቅ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያገዘ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ የአስዋን ግድብን በገደበችበት ወቅት የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ  እንደዚህ ያለ ነገር  ሲሰሩ ሊያማክሩን ይገባ ነበር ብለው ለጠየቁት  ጥያቄ  የግብጽ መሪ የነበረው ገማል አብድል ናሲር  ከአንድ መሪ የማይጠበቅ መልስ  ሰጥተው  እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ  የግብጽ መሪዎች በህዳሴው ግድብ ዙሪያና በአባይ ወንዝ ላይ በህዝቡ ውስጥ አባይ የግብጽ ነው የሚለውን ስር የሰደደ አስተሳሰብ ለማስተካከልና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ይጠበቅባቸዋል፤አንዳንድ የግብጽ መገናኛ ብዙሃንም እውንቱን ከማስረዳት ይልቅ ችግሮችን የሚያባብሱ መረጃዎችን  ሲያሰራጩ እንደሚስተዋሉም  አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ ካስገኘው የስራ እድል፣ የእውቀት ሽግግርና የይቻላል መንፈስ በተጨማሪ ግንባታው ሲጠናቀቅ ሀገራዊ ጠቀሜታዎቹ በርካታ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት  የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሀም ናቸው፡፡ ግድቡ ሰፊ የሆነ የአሣ ሀብት ልማት ለማካሄድ ምቹ እድል ይፈጥራል፤በቱሪስት መስህብነት በማገልገል ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል፤አሁን ያለውን የሀገሪቱን ከ4 ሺህ 2 መቶ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም ወደ 11 ሺህ ለማድረስ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡ በሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠርን ጨምሮ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን በማስገኘት በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል፡፡ ግድቡ በአፍሪካ ደረጃ ህዝብ በአንድ መንፈስና ዓላማ ተባብሮ ሙሉ ድጋፉን የሰጠበት ሥራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሌሎች ለሚሰሩ የድህነት ማስወገጃ ፕሮጀክቶች ትልቅ የሞራል ስንቅም  እንደሆነ  ነው ያብራሩት፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንደስትሪ መር ለማሸጋገር እንዲሁም አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የመሰለፍ ራእይ እንደሚያፋጥን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እስክንድር ነጋሽ ናቸው፡፡ ለታዳሽ ኃይል ስትራቴጂው መሳካት የበኩሉን ሚና በመጫወትም የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የጎላ ድርሻ  እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ ሀገሪቱ ባለፉት 16 አመታት ውስጥ ለሀይል ልማት ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለግማሽ ምእተ አመት ከ300 ሜጋ ዋት የማይበልጥ የነበረውን የኤሌክትሪክ ሃይል ወደ 4ሺህ 2 መቶ ሜጋዋት ማሳደግ ቢቻልም የሀገሪቱ እድገት ከሚፈልገው አንጻር በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ 50 ሺህ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ከውሃ የማመንጨት አቅም እንዳላት በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ 17ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ ለተነደፈው እቅድ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው አቶ እስክንድር የገለጹት፡፡ "ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለእኔ ወደ ነበርንበት ገናና የስልጣኔ ከፍታ የመመለሳችን  አመልካች የሆነ የምህንድስና ጥበብ ውጤት ሆኖ  ነው የሚታይኝ" ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸውታል፡፡ ኢትዮጵያ ከግብርና መር ኢኮኖሚ  ወደ ኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር  በመስራት ላይ በመሆኗ ያሏትን ወንዞች አልምቶ በቂ የኤሊክትሪክ ሃይል ማምረትና መጠቀም ወሳኝ ነው ፡፡ ለዚህም ከአየር ንብርት ጋር ተስማሚ የሆነ  ከፍተኛ ሃይልን የማመንጨት  አቅም ባለው የአባይ ወንዝ ላይ የተፋሰሱን ሀገራት በማይጎዳ መልኩ ግንብቶ መጠቅም የግድ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ የቀድሞ አባቶቹ የሰሩለትን አኩሪ ታሪኮች ወራሽ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ የሚያወርሰው ትልቅ ታሪክ ሰሪ  የሆነበት ነው፤ የዚህ ትውልድ አካል መሆንም እድልኛ ያደርገዋል በማለትም ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡ በየትኛውም የአለም ክፍል ላይ በራሱ መንግስትና ህዝብ የጋራ ርብርብ እንጂ በውጭ ሀገር ድጋፍና ብድር ያደገ ሀገር እንደሌለ ገልጸው የህዳሴው ግድብ በኢትዮጵያውያን በራስ ባለሙያ፣ ገንዘብና እውቀት በመገንባት ላይ የሚገኝ እንደሆንም ረዳት ፕሮፌሰሩ  አስረድተዋል፡፡ "ድሀ ናቸው ብድርና እርዳታ ካላገኙ አይገነቡትም" ሲሉ የነበሩ አንዳንድ የተፋሰሱ ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማትን አመለካከት ጭምር የቀየረና በአለም ላይ ካሉ 10 ከፍተኛ የውሃ ሃይል ማመንጫ ግድቦች አንዱ የሆነውን የህዳሴ ግድብ በራስ አቅም መገንባት እንደሚቻል አስተማሪ ፕሮጀክት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ˝ የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያንን በጋራ ያስተሳሰረ የእናት መቀነት ሆኗል˝ ሲሉም ገልጸውታል ፡፡ እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአባይ ውሃ ላይ ያለውን የመጠቀም መብት ገደብ የሰበረውንና ታላቅ አገራዊ መግባባት የተፈጠረበትን ፣ በሕዝብ ድጋፍ በመስራት በዓለማችን ቀዳሚ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአፍታም ሳይቋረጥ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአቅሙ ድጋፍ ማድረጉን መቀጠል አለበት እንላለን ። ሰላም !!
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም