በምሥራቅ ወለጋ ዞን የግብርናውና የግብይት ሥራዎችን ለማዘመን የተጀመረው እንቅስቃሴ መጠናከር አለበት- ም/ ር/ መስተዳድር ሽመልስ

75
ጥቅምት 8/2012 በምሥራቅ ወለጋ ዞን የግብርናውና የግብይት ሥራዎችን ለማዘመን የተጀመረው እንቅስቃሴ መጠናከር እንዳለበትም የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዞኑ ባደረጉት ጉብኝት ማጠቃለያ ላይ እንዳስገነዘቡት በዞኑ በዘርፎቹ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት መጎልበት አለባቸው። አርሶ አደሩ በክላስተር ማረስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ፣ በገበያ ተፈላጊነት ያላቸውን ምርቶችን በማምረትና በዶሮና በእንስሳት እርባታ ላይ በመሳተፍ ሕይወቱን መለወጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የቡና ኢንቨስትመንትን ለመጀመር መዘጋጀቱን ገልጸው፣ አርሶ አደሩም ከቡና በተጨማሪ  አቮካዶ በማምረት ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡ የግብርና ባለሙያዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በአርሶ አደሩ ማሳ ተባዝተው ተጠቃሚ እንዲያደርጉት አሳስበዋል፡፡ አርሶ አደሩ የጓሮ አትክልት በማምረት በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ከሚመጡ በሽታዎች ራሱንና ልጆቹን መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ትናንት የገበሬዎች ሁለገብ ማሰልጠኛ ማዕከላት ፣ ማሳዎችንና የመኖ ማዘጋጃ ሥፍራዎችን ጎብኝቷል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም