21ኛው የጤና ጉባኤ የዘርፉን ልማት ለማጠናከር የሚያስችሉ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማመላከት ተጠናቀቀ

66
አዲስ አበባ ጥቅምት 7 /2012 ላለፉት አራት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው 21ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ የአገሪቱን ህጻናት የክትባት አገልግሎት ጨምሮ የተለያዩ የዘርፉን ልማት ለማጠናከር የሚያስችሉ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማመላከት ተጠናቀቀ። ጉባኤው ያለፈው ዓመትን የጤና ልማት ተግባራት አፈጻጸምና ጉድለቶችን ከባለሙያዎች፣ ከባለድርሻ አካላት፣ ከማህበራት እና አጋር የልማት ድርጅቶች ጋር ገምግሟል፤ ቀጣይ የትኩረት ቅጣጫዎችንም ተመልክተዋል። በጉባኤው ላይ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ የአገሪቱ የክትባት አገልግሎትን ይመከታል። የአገሪቱ ክትባት አገልግሎት በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ የሚያገኙት ህጻናት 43 በመቶ ብቻ ናቸው። ይህም አመርቂ ባለመሆኑ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ከዚህ ዓመት ጀምሮ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ህጻናት በተቻለ መጠን ክትባት እንዲያገኙ በትኩረት ይሰራል ተብሏል። የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ተሳታፊዎች ቁጥርን አሁን ካለበት 12 ወደ150 ወረዳ በማሳደግ በጤናው ዘርፍ የሚካሄደውን የለውጥ ተግባር ለማጠናከርም ትኩረት እንደሚሰጥ በጉባኤው ላይ ተመልክቷል። ላለፉት 15 ዓመታት በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በጉባኤው ማብቂያ ላይ ገልጸዋል። "ይሁንና በአሁኑ ሰዓት ህብረተሰቡ ካለው ፍላጎት እንዲሁም አገሪቱ ከያዘችው እቅድ አንጻር አመርቂ ስኬት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ቁመና ላይ አይደለም" ብለዋል። በመሆኑም ዜጎች በጤናው ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከዚህ ዓመት ጀምሮ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩን ለማሻሻል የሚያስችሉ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ዶክተር አሚር ተናግረዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩ የሚተገበርባቸውን አካባቢዎች ምቹ ማድረግ፣ መርሃ ግብሩ ሙያንና የትምህርት ደረጃን ያማከለ ማድረግ እንዲሁም ይዘቱንም አሁን ካለው የህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር ማጣጣም በትኩረት የሚሰራባቸው ጉዳዮች ናቸው። ከዚህም ሌላ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን የትምህርት ደረጃ እስከ ዲግሪ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችም ይመቻቻሉ ተብሏል። በጉባኤው ላይ የጤና ባለሙያዎች ፍትሃዊ ተከፋይነት ጉዳይ በስፋት የተዳሰሰ ሲሆን በዚህም ባለፈው ዓመት በመላ አገሪቱ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ለእኩል ስራ ለሁሉም ባለሙያዎች ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲኖር የሚያደርግ ፕሮግራም እንዲቀረጽ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ሚኒስትሩ አውስተዋል። ዘንድሮም የጤና ባለሙያውን እውቀትና ድካም ታሳቢ ባደረገ መልኩ እኩልና ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲኖር የሚያስችለው ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል። በጉባኤው ወረዳን መሰረት ያደረገ የ2012 ዓ.ም የጤና ዘርፍ እቅድ ላይ በቁርጠኝነት ለመስራት የጤና ሚኒስቴር ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር የጋራ ስምምነት ተፈርሟል፤ የቃልኪዳን ስነ-ስርዓትም ተካሂዷል። 21ኛው የጤናው ዘርፍ አመታዊ ጉባኤ “የዜጎች ጤና ለአገር ብልጽግና” በሚል መሪሃ ሃሳብ ለተከታታይ አራት ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም