የመደመር ፍልስፍና መጽሐፍ ነገ በሰመራ እና ሐረር ከተሞች ይመረቃል

112
ሰመራ/ሐረር ኢዜአ ጥቅምት 7/2012፡-የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመደመር ፍልስፍና መጽሐፍ በአፋር እና ሐረሪ ክልሎች ደረጃ ነገ በሰመራና ሐረር ከተሞች እንደሚመረቅ ተገለጸ። የአፋር ክልላዊ መንግስት  ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ አህመድ ከሎይታ እንዳሉት ለመጽሐፉ የምረቃው ስነ ስርዓት ሲደረግ የቆየው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል። በዚህም የአዳራሽ ዝግጅትና በስነስርዓቱ የሚሳተፉ ሰዎች እንዲሁም የመጽሐፍት አቅርቦት ስራ ተመቻችቷል። "በምረቃው ስነ ስርዓቱም ከክልሉ  ከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች ጨምሮ  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ" ብለዋል። መጽሐፉ የመደመር ፍልስፍና ከአመራሩ እስከ ህብረተሰቡ ድረስ ወጥ የሆነ ግንዛቤን በማስጨበጥ  የተጀመረውን ክልላዊና ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ለማፋጠን እንደሚግዝ ተመልክቷል። በሌላ በኩል የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንደገለጸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው “መደመር” መጽሐፍ ነገ ይመረቃል። በጽህፈት ቤቱ  ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዲኒር ዩስፍ  በመደመር እሳቤ ላይ የተፃፈው የዶክተር አብይ መጽሐፍ የሚመረቀው በክልል ደረጃ  መሆኑን ገልጸዋል። በሐረር ከተማ በሚገኘው የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሚከናወነው የምረቃ ስነስርዓት  የክልሉ መንግስት ስራ ኃላፊዎች ፣ የስነ ጽሑህ ባለሙያዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣የሀገርሽ ማግሌዎች፣ወጣቶች እና ሌሎችም የሀብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ለመጽሐፉ ምረቃው ስነ ስርዓት  ዝግጅት አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ የማመቻቸቱ ስራ መቀጠሉንና  ስለመደመር የተጻፈው አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት ዙሪያ ለተሳታፊዎች ገለፃ እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። መጽሐፉ  በአማርኛ፣አፋን-ኦሮሞ እና እንግሊዘኛ  ቋንቋዎች  እንደተጻፈና ከመጽሐፉ  ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለትምህርት ልማት እንደሚውል ጠቁመዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም