በአማራ ክልል ለ320 ሺህ ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ከትባት ሊሰጥ ነው

75
ባህርዳር ኢዜአ ጥቅምት 7 / 2012 ዓ.ም  በአማራ ክልል ከ320ሺህ በላይ ልጃገረዶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ለመስጠት የሚያስችል ዘመቻ ሊያካሄድ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ ። በሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ዕድሜያቸው 14 አመት የሞላቸው ሁሉንም በክልሉ የሚገኙ ልጃገረዶችን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ተብሏል ። በቢሮው የጤና አጠባበቅ ትምህርትና ፕሮሞሽን ስነ-ተዋልዶ ጤና ባለሙያ ወይዘሮ የሺወርቅ አሞኘ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ ለሁለተኛ ጊዜ የሚሰጠው የማህፀን ጫፍ ካንሰር ክትባት ከጥቅምት 10 እስከ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። በዘመቻውም እድሜያቸው 14 አመት ለሞላቸው 320ሺ231 ልጃገረዶችን የአገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተይዞ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል ። ክትባቱ በክልሉ በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፣ በመንግስት ጤና ተቋማትና ለክትባት ተመርጠው በተዘጋጁ አማካይ ቦታዎች እንደሚሰጥም አስረድተዋል ። በሽታው የሚመጣው ” ሂውማን ፓፒሎማ ” በሚባል ቫይረስ አማካኝነት በመሆኑ የክትባቱ መሰጠት በሽታውን ቀድሞ በመቆጣጠር የሴቶችን ህይወት ለመታደግ ያስችላል ብለዋል ። በዘመቻ የሚሰጠው ክትባት ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያመጣ ጠቁመው በሽታውን መከላከል የሚቻለው አንዲት ልጃገረድ በአንደኛና ሁለተኛ ዙር የሚሰጠውን ክትባት በአግባቡ መውሰድ ስትችል ነው ። በዚህም የመጀመሪያው ዙር ክትባት የሚወስዱ ልጃገረዶች ሁለተኛውን ዙር በመጪው ሚያዝያ ወር 2012 መውሰድ እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል ። ቢሮውም ቀደም ሲል ክትባቱን ለሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት ስለክትባቱ ጠቀሜታ የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለህብረተሰቡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችና ህዝብ በብዛት በተሰበሰበባቸው ቦታዎች ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ። የማህፀን ካንሰር ለሴቶች አስከፊ በሽታ በመሆኑ መምህራን ፣  የጤና ባለሙያዎች ፣የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ፣ ወላጆችና ባለድርሻ አካላት ተገንዝበው በዘመቻ ው ሁሉም ልጃገረዶች ክትባቱን እንዲያገኙ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል ። በክልሉ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ መልክ የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ ካደረጉ 8ሺ698 እናቶች መካከል 1ሺ131 የቅድመ ካንሰር በሽታ እንደተገኘባቸው ባለሙያዋ ተናግረዋል ። እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው አመት በተሰጠው የማህፀን ጫፍ ካንሰር ክትባት ዘመቻ በክልሉ ከ276 ሺህ 400 የሚበልጡ እድሜያቸው 14 አመት የሞላቸው ልጃገረዶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸው ታውቋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም