በምስራቅ አፍሪካ ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት ለማምጣት አገሮች ውስጣዊ ተቋሞቻቸውን በቅድሚያ ማጠናከር ይገባቸዋል

50
ኢዜአ ጥቅምት 07/2012 ዓ.ም  በምስራቅ አፍሪካ ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት ለማምጣት የአከባቢው አገሮች ውስጣዊ ተቋሞቻቸውን በቅድሚያ ማጠናከር እንደሚገባቸው ተገልጿል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ከአካባቢያዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ጋር ያነጻጸረው የምክክር መድረክ ዛሬ ቀጥሎ ውሏል። በጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሃሪይ ቬርሆቨን የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልጸው የውስጥ መከፋፈል አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል። ችግሮቹ ታሪካዊና አንዳንዱም ወቅታዊ ሁኔታን ተንተርሶ የተቀሰቀሱ መሆኑን ገልጸው፤ ''እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የውስጥ ተቋሞችን ጠንካራ ማድረግ ያስፈልጋል'' ብለዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አገሮቹ በመሪዎች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሥራ ከመሥራት ይልቅ በመርህ ላይ በተመሰረቱ የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት ተቋማት መመራት ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነ ግን አንዱ ሲመጣ ከዚህ ቀደም የነበረውን በማፍረስና ሌላ አሰራር በማስፈን የሚካሄደው ሥራ በቀጠናው ላይ ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት ለማምጣት የሚሰራውን ስራ አዳጋች እንደሚያደርገው ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት የቀጠናው አገሮች የተለያዩ የለውጥ ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን አስታውሰው ተቋማትን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ኃሳባቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያም የቀጠናውን አገሮች በማቀራረብና ትብብር እንዲፈጠር በማድረግ ያላትን ትልቅ ድርሻ ከግምት በማስገባት ሚናውን በእጅጉ መወጣት እንዳለባት ተናግረዋል። ኢትዮጵያም በቀጠናው ጠንካራና ትልቅ ሕዝብ የያዘች አገር በመሆኗ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) ማዕቀፍ ሥር ከፍተኛ ሥራ መሥራት እንደምትችል በመግለጽ ኃሳብ ሰጥተዋል። በመድረኩ ከዚህ ጎን ለጎን በቀጠናው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በትበብርና በተለይም በባለብዙ ወገን አጋርነት ላይ ያተኮረ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ አጽንዖት ተሰጥቶታል በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን፣ በሱዳንና በሶማሊያ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ እየታየ ያለው አዎንታዊ ለውጦች ለቀጣይ የቀጠናው ትብብር ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተጠቁሟል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መከካል የተደረሰው የሰላም ሥምምነት ደግሞ ትልቅ ውጤት መሆኑ ታምኖበታል። ፓዝ ፋይንደር በተባለው ግብረ-ሰናይ ተቋም የውጭ ግንኙነት ከፍተኛ የጥናት ባለሙያው ማት ብርይዳን ደግሞ ''በቀጠናው በቅድሚያ ሰላም መረጋገጥ መቻል አለበት'' ብለዋል። በዚህም ላይ የቀጠናው አገሮች በዘርፉ የሚያወጡትን እቅድና ስትራቴጂ ተመጋገቢና ለጋራ ጥቅም አብሮ መሥራት የሚያስችል መሆን እንዳለበት ምክረ ኃሳብ ሰጥተዋል። በቀጠናው የግጭትና የአለመግበባት ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል መፍትሄ ኢጋድን በመሰሉ መድረኮች ማቅረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት ተቋማትንም ማጠናከርና ማጎልበትም መንግሥታት ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት። ለሁለት ቀናት ሲካሄደ የቆየው ይኸው የኢትዮጵያ ውጭና የደህንነት ፖሊሲ የምክከር መድረክ ዛሬ ይጠናቀቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም