የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ በመቀየር ላይ የነበረ ባለሙያ በደረሰበት የኤሌክትሪክ አደጋ ህይወቱ አለፈ

160
ጥቅምት 7/2012 በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ በመቀየር ላይ የነበረ ባለሙያ በደረሰበት የኤሌክትሪክ አደጋ ህይወቱ አልፏል። ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በተለምዶ ሾላ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ከቀኑ 7 ሰአት ገደማ ከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ በመቀየር የነበረ ባለሙያ ድንገት ሃይል በመለቀቁ የተነሳ በደረሰበት የኤሌክትሪክ አደጋ ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎቱን ለማሻሻልና የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ያረጁ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችና ተሸካሚ ምሰሶዎችን በአዲስ መልክ የመቀየር ተግባር እያከናወነ ይገኛል። ስራውንም በተቋራጭነት የቻይናው የኤሌክትሪክ ሃይል ኩባንያ ፓወር ቻይና በመስራት ላይ እንደሚገኝም ይታወቃል። ህይወቱ ያለፈው ወጣት ለፓወር ቻይና ተቀጥሮ የሚሰራ እንደሆነና የኤሌትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ እየቀየረ ሳለ ከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር በጥንቃቄ ጉድለት ሃይል ተለቆ ህይወቱ እንዳለፈ የአይን እማኞች ገልጸዋል። ህይወቱ ያለፈው ወጣት አስክሬኑ ለምርምራ ወደሆስፒታል መላኩን ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በፊት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችና ተሸካሚ ምሰሶዎችን የመቀየር ስራ ላይ በሚደርሱ አደጋዎች ሰራተኞች ህይወታቸው እንደሚያልፍና የአካል ጉዳት እንደሚደርስባቸው ይታወቃል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2011 ዓ.ም በጀት እቅድ አፈጻጸምና የ2012 ዓ. በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር። በወቅቱ የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በተያዘው በጀት ዓመት ከሚሰሩ ስራዎች መካከል ከኤሌክትሪክ ጋር በተያያዘ በሰው አካልና ህይወት ላይ የሚደርሰውን አደጋና ጉዳት መቀነስ እንደሆነ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ዳይሬክተሩ ይሄን በገለጹ በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ ዛሬ ከኤሌክትሪክ ጋር በተያያዘ በደረሰ አደጋ የአንድ ወጣት ህይወት አልፏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም