በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ነባር ማህበራዊ እሴቶች ለሰላም ግንባታ እንዲዉሉ ይደረጋል

72
ጥቅምት 7/2012 በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ነባር ማህበራዊ እሴቶችን በመጠቀም ሰላም የማስፈን ተግባር በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ። የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት 'ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ' ጋር በመተባበር ''ለአገራዊ ችግር አገራዊ መፍትሔ'' በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት እያደረገ ይገኛል። ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎች እየተሳተፉበት የሚገኘው ይኸ ውይይት ማሕበራዊ እሴቶችን ለሰላም ግንባታ መጠቀምን ያለመ ነው። በጉዔው የተናገሩት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙሪያት ካሚል እንዳሉት "ማህበራዊ እሴቶቻችን በፍጥነት እየተሻረሸሩ" እንደሚገኙ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ከሌሎች ችግሮች ጋር ተዳምሮ አሁን እየታጣ ላለው ሰላምና ደህንነት መጓደል ዋነኛ መንስኤ ነው ብለዋል። ከሁሉም በላይ የሰላምን ችግር ለመፍታት የጎለበቱ ማህበራዊ እሴቶችን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል  እንደሚሰራ በማከል። በተለይ ደግሞ የአገር ሽማግሌዎች ለአብነት በ1997 ዓ.ም አጋጥሞ የነበረውን የሰላም ችግር ከመፍታት አንስቶ እስካሁን ብዙ ውጤታማ ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። አገሪቷ ሽግግር ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ እያጋጠመ ያለውን ችግር በልኩ ለመፍታት ሁሉም ሚናውን እንዲወጣም አሳስበዋል ሚኒስትሯ። ''በዚህ ወቅት ተቀራርበንና ተወያይተን ችግራችንን መፍታት ነው የሚያስፈልገው'' ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ የአገር ሽማግሌዎች በዚህ ላይ እንዲያግዙ ጠይቀዋል። እነዚህ ማህበራዊ እሴቶች ሳይበረዙ ለትውልድ ይተላለፉ ዘንድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ይወጠም ብለዋል ሚኒስትሯ። የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፣ ኃይማኖቶችና ባሕሎች መስተጋብር ያላት አገር መሆኗን ይጠቅሳሉ። ይህ ሆኖ ሳለ "ታሪክን መሰረት ያደረጉ አላስፈላጊ ንትሮኮች አገሪቷን ወደ አደገኛ ችግር እየወሰዷት ይገኛሉ" ብለዋል። ከሁሉም በላይ ግን ልዩነት ላይ ያተኮረ ትርክት እንዲሁም የወጣቶች ስራ አጥነት የሰላሙን ጉዳይ አሳሳቢ እድርገውታል ነው ያሉት። በመሆኑም የአገር ሽማግሌዎች እንዲህ እይነቱ ችግር ወደ ከፋ ሁኔታ አምርቶ የዜጎችን ህይወት እንዳይቀጥፍ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም እንዲሁ አሁንም ቢሆን በያሉበት አካባቢ ሰላም እንዲኖር በጠንካራ ሁኔታ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል። ወደ ፊትም ይህንኑ ተግባር በማጠናከር አገሪቷ ወደ ተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንድትመጣ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም