ለኖቤል ሽልማቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋናና የዕውቅና መርሃ-ግብር ይካሄዳል

64
አዲስ አበባ ጥቅምት 7 /2012 ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተሰጠውን የሰላም የኖቤል ሽልማት ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሽልማቱ መገኘት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ዕውቅና እንደሚሰጥ ሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማትን ማግኘታቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ሰላም ሚኒስቴር ለዚህ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና አስተዋጽኦ ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና በየደረጃው ላሉ አካላት ዕውቅና የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለ20 ዓመት የዘለቀውን አለመግባባት በሰላም በመቋጨታቸውና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለሽልማቱ እንዲታጩ አድርጓል። ከዚህ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡ በመቶ ቀናቸው በአገሪቷ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ በማድረጋቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በነጻ መፍታታቸው ብሎም በሰላማዊ መንገድ እንዲሰሩ ማድረጋቸውም ቀላል ግምት አልተሰጠውም። ከዚህ ባለፈም በአገሪቷ በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ስለ ሰላምና ይቅርታ ያደረጉት ንግግር ብሎም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የወሰኑት ውሳኔም ለዚህ ሽልማት እንዲበቁ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። የኖቤል የሰላም ሽልማቱ ከዓለም ዓቀፍ እውቅናው በተጨማሪ 900 ሺህ የአሜሪካን ዶላር  ሽልማት  ያለው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጪው ታኅሣሥ ኦስሎ ተገኝተው ሽልማታቸውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመጪው እሁድ በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄደው የዕውቅናና የምስጋና መርሃ-ግብሩ ላይም ከአምስት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከእነዚህም ውስጥ ከፌዴራልና ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ የውጭ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እንዲሁም የሙያና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ይገኛሉ። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል ሽልማትን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን የአገር ውስጥና የውጭ አገር መሪዎችና ተቋማትም የደስታ መልዕክታቸውን ለመላ ኢትዮጵያውያን ሲያስተላልፉ እንደነበር የሚታወስ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም