በትግራይ ክልል የተጀመረው አዲስ የወረዳ አደረጃጀት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ያግዛል...ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

127
ጥቅምት 7/2012 በትግራይ ክልል አዲስ የወረዳ የአደረጃጀት ስራዎችን በማጠናከር የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርእስ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ። የክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ ዘመን 17ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል። ምክትል ርእስ መስተዳድሩ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የ2012 በጀት አመት አመታዊ እቅድ የትኩረት አቅጣጫዎች ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ እንደገለጹት በክልሉ ምሁራን ተጠንቶ የቀረበው የወረዳዎች አደረጃጀት የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ በሚያስችል መልኩ ተግብራዊ ይደረጋል። አዲሱ የወረዳ አደረጃት ህዝቡ ተወያይቶበት በምክር ቤቱ የሚፀድቅ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ደብረፅዮን ካለፈው ዓመት ጀምሮ በገጠር ቀበሌዎች የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ቋሚ ሰራተኞች በመመደባቸው በመሬት አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን እየፈቱ መሆናቸውን ተናግረዋል። አሰራሩ ዘንድሮም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀው በክልሉ ያሉት የመንግስት መስሪያ ቤቶች አደረጃጀትም ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ ስራ እንዲሰሩ በአዲስ መልክ ለማደራጀት የሚያስችል ጥናት እንደሚጀመር ገልጸዋል። የክልሉን ገቢ ለማሳደግ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ረገድ የማኑፋክቸሪንግና የአገልግሎት ዘርፉን ከግብርናው በተሻለ መልኩ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል። በበጀት አመቱ 258ሺህ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል መፍጠርና ከስድስት ቢልዮን ብር በላይ የብድር አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስረድተዋል። በበጀት ዓመቱ ከግብር እና ከታክስ የሚሰበሰብ ገቢ ወደ ስድስት ነጥብ ስድስት ቢልዮን ብር ለማሳደግ መታቀዱንም ገልጸው እቅዱን ለማስፈፀም በየደረጃው ያለው አመራርና ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያቸውንም አስተላልፈዋል። የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ሩፋኤል ሸፋረ በበኩላቸው ባቀረቡት የስራ እቅድ ላይ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ከሲቪክ ማህበራትና ከአጎራባች ክልሎች ጋር የጀመረውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል። ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማጠናከርም ከሲቪክ ማህበራት ጋር የተጀመረውን ግንኙነት በማጠናከር ስራዎችን በጋራ ለማከናወን መታቀዱን ገልጸው “በክልሉ በየደረጃ የሚገኙ የምክር ቤት አባላትን አቅም ከማጠናከር በተጨማሪ በአስፈፃሚው አካል የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥርም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል። ከአሁን ቀደም ከአፋር ክልል አዋሳኝ ወረዳ ምክር ቤቶች ጋር የተጀመረውን የጋራ ግንኙነት ወደ ህዝብ ለህዝብ የማውረድና ወደ አማራ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች ለማስፋት የክልሉ ምክር ቤት ፍላጎት መሆኑንም አቶ ሩፋኤል ተናግረዋል።ለሁለት ቀናት በሚቀጥለው የምክር ቤቱ ጉባኤ የዛሬ ውሎ አባላት በምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ በቀረበው አመታዊ የስራ እቅድ ላይ ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም