በኮንታ ልዩ ወረዳ በመሬት መንሸራተት የሞቱት ሰዎች አስከሬን የማውጣት ስራ ተጠናቀቀ

69
ጅማ ጥቅምት 7/2012 በኮንታ ልዩ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጠፍተው የነበሩ 22 ሰዎች አስከሬናቸው ሙሉ በሙሉ በመገኘቱ ፍለጋው መጠናቀቁን የወረዳው የህዝብ ግንኝነት ፅህፈት ቤት ገለፀ ። በልዩ ወረዳው ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሊት ላይ በደረሰው የመሬት መንሸራተት 22 ሰዎች በናዳ ተውጠው እንደነበር ይታወሳል ። በናዳው ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች ህይወት ለመታደግና ከሞቱም አስከሬናቸው ለማውጣት ከመስከረም 3 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ላለፉት 4 ቀናት ሲካሔድ የነበረው ፍለጋ ትናንት የመጨረሻዎቹ 2 ሰዎች አስከሬን በማውጣት ተጠናቅቋል ። የወረዳው አስተዳደር የህዝብ ግንኝነት ኃላፊ አቶ ፋሲካ ሙሉጌታ እንደገለጡት በእልህ አስጨራሹ ፍለጋ የ22ቱ ሰዎች አስከሬን በማውጣት ተጠናቅቋል ። የወረዳው አስተዳደር የአካባቢው ህብረተሰብ በአደጋው ምክንያት የሞቱ ሰዎች አስከሬን ለማውጣት በተካሔደው ርብርብ ላበረከተው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል፡፡ በተለይም ሳሊኒ ኢንምፕርጂሎ የተባለ ፕሮጀክት 40 ሰራተኞችና እስከባተር በመመደብ ጉልህ እገዛ ማበርከቱን ኃላፊው ገልፀዋል ። የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ በፍለጋው ለተሳተፉ ተቋማትና ሲቪክ ማህበራት የወረዳው አስተዳደር ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል ። የወረዳው አስተዳደር በአደጋው የተፈናቀሉ 481 አባወሯና እማዋሯዎች መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት መንግስታዊና መንግስታዊ ያለሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል ። በአደጋው ከጠፋው ህይወት በተጨማሪ 27 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙንም ኃላፊው አያይዘው ገልፀዋል ። በወረዳው ከዚህ አደጋ በፊት ሶስት ጊዜ በደረሰው የመሬት መደርመስና በጎርፍ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ተገልፆ እንደነበር ይታወሳል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም