በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ግብፅ ላቀረበችው አዲስ ሃሳብ በኢትዮጵያ በኩል ቴክኒካዊ መልስ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው

122
አዲስ አበባ ጥቅምት 7 /2012  በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ዙሪያ ግብፅ ላቀረበችው አዲስ ሃሳብ በኢትዮጵያ በኩል ቴክኒካዊ መልስ መስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ። የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ ለካቢኔ አባላትና ባለድርሻ አካላት ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ የኢትዮጵያና የግብፅ ወቅታዊ አቋም ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል። የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ላይ ያቀረበችው አዲስ ሃሳብ ቀደም ሲል በሶስቱ ሀገራት መካከል የተፈረመውን የአባይ ውሃ አጠቃቀም የመርህ ስምምነት የጣሰ ነው ። ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅ፣ የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት በሰባት አመት እንዲሆን የሚል ግብፅ አዲስ አቋም ማራመድ ጀምራለች። የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ግድቡ ዋና ስራው ውሃ መልቀቅ ብቻ እንዲሆን የሚልም አዲስ ሃሳብ አምጥታለች። ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ሉአላዊነቷን የሚጥስ በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል። በግብጽ በኩል የቀረቡ ሀሳቦች ላይ ቴክኒካዊ መልስ መስጠት የሚቻልባቸው አደረጃጃቶችን በአዲስ መልኩ የማዋቀር ስራ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የግድቡን ግንባታ ለመጀመር በወጠነችበት ወቅት ግብፅ ግንባታው እንዳይከናወን የተለያዩ ማሰናከያ ሀሳቦችን ስታራምድ መቆየቷን ያስታወሱት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ አሁን ላይ ደግሞ የተለያዩ አዳዲስ ሀሳቦችን እያራመደች መሆኑን ገልጸዋል። የግድቡ ግንባታ እየተገባደደ ባለበት በአሁኑ ወቅት በግብጽ በኩል የሚደረገው ግፊት እየጨመረ የሚመጣ በመሆኑ አንድነት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ከካቤኔና ባለ ደርሻ አካላትም የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን ማከናወን እንደሚኖርባትም ተናግረዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሮአዊ መብት በሚመጥን መልኩ የመደራደር ሚናዋን በተመለከተ ጥያቄ አንስተዋል። በኢትዮጵያ በኩል ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ ሊነሱ የሚችሉ ስጋቶችን በቅድሚያ በመለየት የመደራደር አቅሟን ማጎልበት ነበረበት ሲሉም ተናግረዋል። የሴቶችና ህጻናትና ሚኒስትር ወይዘሮ የአለም ጸጋዬ በበኩላቸው ግብጽ በአሁኑ ወቅት አዲስ ሀሳብ ለማቅረብ ያበቃት ምክንያት በግልጽ እንዲብራራ ጠይቀው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እንዳሉት የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የቴክኒካል እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። በግብፅ በኩል አዲስ ሀሳብ የተነሳው የግድቡ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ በኩል በግድቡ ዙሪያ የሚደረገውን የዲፕሎማሲ እንቅሰቃሴ የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም