በታዳጊ አገሮች 192 ሚሊዮን ዜጎች ስራ አጥ ሲሆኑ 730 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በቂ ገቢ አያገኙም

49
ጥቅምት 7/2012 በታዳጊ አገሮች 192 ሚሊዮን ዜጎች ስራ አጥ ሲሆኑ 730 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ስራ ቢኖራቸውም በቂ ገቢ እንደማያገኙ የዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት (አይኤልኦ) ገለጸ። ድህነትን ለማጥፋት ለዜጎች የሚደረገው የገቢ ድጋፍ ከስራ ገበያ ፖሊሲዎች ጋር አጣምሮ መተግበር እንደሚገባም አመልክቷል። አይኤልኦ ትናንት የተከበረውን ዓለም አቀፍ ድህነትን የማጥፋት ቀን አስመልክቶ "በአገሮች ተጨባጭ ሁኔታ ምቹ ስራ የማግኛ መንገዶችን ማስተዋወቅ" በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን የጥናት ሪፖርት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል። ሶስት አመት የፈጀው ይህ ጥናት ድህነትን ለማጥፋት ለዜጎች የሚደረገው የገቢ ድጋፍ ከስራ ገበያ ፖሊሲዎች ጋር አጣምሮ መተግበር ውጤታ እንደሆነ አሳይቷል። ለዚህም ጥናቱ በሞሪሺየስና ኡሯጓይ ድህነትን ለማጥፋት የዜጎች የገቢ ድጋፍና የስራ ገበያ ፖሊሲዎች ጥምር ትግበራን ተመልከቷል። አይኤልኦ በድህነት ውስጥና በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ 192 ሚሊዮን ዜጎች ስራ አጥ እንደሆኑና 730 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ስራ ያላቸው ቢሆንም የሚያገኙት ገቢ ከድህነት ለመውጣት በቂ እንዳልሆነ ይገልጻል። ስራ ማግኘት ከድህነት መውጫ ዋንኛ መንገድ እንደሆነና የስራዎች ተደራሽነት፣ ምቹ ስራን ማግኘትና ምቹ የስራ ሁኔታ በተፈጠረበት ቦታ መስራት አሁንም ፈተና እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል። አይኤልኦ የጥናት የስራ ክፍል የስራ ገበያ አዝማሚያና የፖሊሲ ግምገማ ንዑስ የስራ ክፍል ተጠባባቂ ሃላፊ ሚስ ቬሮኒካ እስኩዴሮ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ድህነትን ለማጥፋት ለዜጎች የገቢ ድጋፍና የስራ ገበያ ፖሊሲዎችን ለየብቻ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የገቢ ድጋፍ ብቻ ማድረግ ዜጎች ከሚያገኙት የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ ዜጎች በዘላቂነት ከድህነት እንዲወጡ እንደማያደርግና የስራ ገበያ ፖሊሲዎችን ብቻ መተግበር ጊዜ የሚወስድና ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስወጣ ነው ብለዋል። በኡራጓይና ሞሪሺየስ የሁለቱ ጥምር ትግበራ ዜጎች በዘላቂነት ከድህነት እንዲወጡ እያደረገና የኑሮ ሁኔታቸው እየተሻሸለ መሆኑን ጠቅሰዋል። የስራ ገበያ ፖሊሲዎች ዜጎች የክህሎት ስልጠና፣ የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ኤጀንሲዎች የስራ እድል እንዲያመቻቹላቸው ማድረግ፣ የስራ አጥነት ኢንሹራንስ እንዲኖራቸው የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል። የበለጸጉ አገሮች ለዜጎች የሚደረገው የገቢ ድጋፍ ድጋፍ ከስራ ገበያ ፖሊሲዎች ጋር አጣምረው እያከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ጥምር ትግበራው በታዳጊ አገሮች ውጤታማነቱን ለማረጋጋጥ ተጨማሪ ጥናት ማድረግ ስለሚያስፈልግ አይኤልኦ ከሚመለከታቸው ተቋማት እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የአይኤልኦ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሚስ ሲንቲያ ሳሙኤል-ኦሎንጁዎን ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት መደበኛ ባልሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰማሩትን ወደ መደበኛ እንዲመጡ ማድረግ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል። እ.አ.አ በ2017 በተደረገ ጥናት መሰረት ከ80 በመቶ በላይ ዜጎች መደበኛ ባልሆኑ የስራ ዘርፎች እንደሚሰሩና በመደበኛ ባልሆኑ የስራ ዘርፎች የሚሰሩ ወጣቶች 95 በመቶ ድርሻ እንደሚይዙና አምስት በመቶ ብቻ ዜጎች መደበኛ ስራ ላይ እንደተሰማሩ ጠቅሰዋል። መደበኛ ያልሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ መስራት ዜጎችን ከድህነት ማውጣት እንደማይችልና መብታቸውን እንደማያስከብር ገልጸዋል። አፍሪካውያን መደበኛ ካልሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ወጥተው በመደበኛ ስራዎች በስፋት ካልተሰማሩ አፍሪካን ከዘላቂ ድህነት ማውጣት እንደማይቻልና በመገንዘብ መንግስታት መስራት እንዳላባቸው ነው ሚስ ሲንቲያ ያስረዱት። በአፍሪካ የማህበራዊ ዋስትና ያላቸው ዜጎች 17 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ብቻ እንደሆነና ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና እንዲያገኙና መብታቸው እንዲከበር መስራት ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነም አስረድተዋል። እ.አ.አ በ2020 በሚካሄደው የአፍሪካ የሰራተኛና ማህበራዊ ዋስትና የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የጥናት ሪፖርቱ ለመንግስት አካላት እንደሚቀርብም ጠቁመዋል። የአፍሪካ ህብረት የማህበራዊ ጉዳዮች የስራ ክፍል የስራ ገበያና ስደተኞች ጉዳይ ንዑስ የስራ ክፍል ሃላፊ ሚስተር ሳቤሎ ምቦካዚ ይፋ የተደረገው የጥናት ሪፖርት የአፍሪካ አገሮች እንደ መነሻ ሀሳብ ወስደው ወደ ጥምር ትግበራው እንዲገቡ ያስችላል ብለዋል። በቀጣይ ህብረቱ ዜጎች ምቹ ስራ እንዲያገኙ የፋይናንስ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ተቋማዊ አቅምን ማጠናከርና የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን ያካተት የቅንጅት ስራ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ዜጎችን ከድህነት ለማውጣትና ምቹ ስራ እንዲያገኙ እየሰራች መሆኗን በመድረኩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን በመወከል የተገኙት አቶ አበበ ሃይሌ ገልጸዋል። የጥናት ሪፖርቱ ኢትዮጵያ በግብአትነት በመውሰድና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ለቀጣይ ስራ እንደ መነሻ እንደምትቀመጥበት ተናግረዋል። አይኤልኦ ትርጓሜ መሰረት ምቹ ስራ የስራ መብት፣ ፍትሐዊ ገቢ፣ የስራ ደህንነት፣ ስራ የመፍጠር ክህሎት፣ ማህበራዊ ዋስትና መንግስትና የስራ ማህበራት በጋራ በመሆን ሰራተኞች ጥቅማቸው እንዲከበሩ የሚያስችሉ ስራዎችን ማከናወን በውስጡ የያዘ መሆን አለበት። ዓለም አቀፍ ድህነትን የማጥፋት ቀን እ.አ.አ ከ1992 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አማካኝነት በየዓመቱ ይከበራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም