ደኢህዴን ከክልሉ ውጪ የሚገኙ አባላቱ ለውጡን እንዲደግፉ እየሠራ ነው

79
ጥቅምት 7/2012 ከደቡብ ክልል ውጪ የሚገኙ አበላት እና ደጋፊዎቹ በሚኖሩባቸው ክልሎች ሃገራዊ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በንቃት እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን የደኢህዴን ከክልል ውጪ የሚገኙ አደረጃጀቶች ሃላፊ አቶ ኑረዲን ሃሰን ገለጹ፡፡ ንቅናቄው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ አባላት እና ደጋፊዎቹ ጋር በአሶሳ ከተማ ተወያይቷል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ከክልል ውጪ አደረጃጀት ሃላፊ አቶ ኑረዲን ሃሰን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ንቅናቄው ከደቡብ ክልል ውጪ ከ40 ሺህ በላይ አባላትና ደጋፊዎች አሉት፡፡ እነኚህ አባላቱ በሚኖሩባቸው ክልሎች ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ የሚያስተባብሩ 11 አደረጃጀቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ አደረጃጀቶቹ የንቅናቄውን አባላት በማስተባበር ክልሎቹን የሚመሩ ፓርቲዎች የሚያከናውኗቸው የሠላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር እቅዶቻቸውን አፈጻጸም ተሳታፊ እየሆኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በህብረተሰቡ ትግል የተገኘው ሃገራዊ ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አባላቱ በሚገኙበት ቦታ ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ አደረጃጀቶቹ ግንዛቤያቸውን ከማሳደግ ጀምሮ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሃገር ተዘዋውረው የመሥራት ህገ-መንግስታዊ መብታቸው የሚከበረው ሠላም ሲኖር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ንቅናቄው ሃገሪቱ ሠላም እንድትሆን ሲሠራ መቆየቱን የሚናገሩት ሃላፊው አሁንም አባላቱ በየክልሎች የተከሰቱ ግጭቶች እንዲፈቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀራረብ እየሠሩ መሆናቸውን አቶ ኑረዲን አክለዋል፡፡ በውይይቱ የተሳተፉ አንዳንድ የድርጅቱ አባላት በበኩላቸው በሚኖበት ክልል ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻው ጋር በመቻቻልና መቀናጀት ለአካባቢያቸው መለወጥ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የግብርና ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ አድራ ሱልጣን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚያከናውኗቸው የልማት ሥራዎች ሁሉ  ሃገራዊ ለውጡን በማስቀጠል ስሜት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የደቡብ ክልል ተወላጅና የንቅናቄው አባል የሆኑት አስር አለቃ ታደሰ መኩሪያ በበኩላው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ30 ዓመታት በላይ መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ የክልሉ ብሎም የሃገሪቱ ሠላም እንዲጠናከር ከክልሉ ህዝብ ጋር ያላቸውን አንድነት በማጠናከር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ለግማሽ ቀናት የተካሄደው ውይይት በግንባሩ የ2011 እቅድ አፈጻጸም ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ላይ ያተኮረ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም