በባሌ ዞን 49 ሺህ 629 ሄክታር የስንዴ ቡቃያ ከዋግ በሽታ ነጻ ተደረገ

47
ጎባ ኢዜአ ጥቅምት 7 ቀን 2012 በባሌ ዞን 49 ሺህ 629 ሔክታር የስንዴ ቡቃያ ከዋግ በሽታ ነጻ መደረጉን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ኦሊቃ ለኢዜአ እንደገለጹት የስንዴ ቡቃያው ነጻ የተደረገው በአምስት ወረዳዎች በበሽታው ተጠቅቶ ከነበረው 49 ሺህ 758 ሄክታር ውስጥ ነው። "በሽታውን ለመቆጣጠር  4 ሺህ 600 ሊትር የፀረ ዋግ መድኃኒት ጥቅም ላይ ውሏል" ብለዋል። በወረዳዎቹ ከ60 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በበሽታው ቁጥጥር ስራ መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል ። በቀሪው 129 ሄክታር የስንዴ ቡቃያ ላይ በሽታውን የመቆጣጠር ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ። የጎባ ወረዳ ነዋሪ   አርሶአደር አብዲሳ ከተማ ከባለሙያ በተሰጣቸው ምክር መሰረት መድሀኒት በመርጨት በሽታውን መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል ። "ማሳየን በመንከባከብና መድሀኒት በመርጨት በሽታው በቡቃያ ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርሰ መከላከል ችያለሁ" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ሁሴን ከማል ናቸው። በዞኑ በ2011/ 2012 ምርት ዘመን መኽር ወቅት ታርሶ በተለያየ የሰብል ዘር ከተሸፈነው 335 ሺህ ሄክታር መሬት 10 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም