ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ቡናዋን በቻይና ገበያ ለማስተዋወቅ ተዘጋጅታለች

61
ጥቅምት 7/2012 ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ቡናዋን በቻይና ገበያ ለማስተዋወቅና የገበያ አማራጯን ለማስፋት ከጥቅምት 25 እስከ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በሻንጋይ ከተማ በሚካሄደው የቻይና 2ኛው አለም አቀፍ የአስመጪዎች ኤክስፖ ለመሳተፍ መዘጋጀቷን ዥንዋ ዘግቧል። ኢትዮጵያ የወጪ ንግዷን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥታ እየተንቀሳቀሰችባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል ቡና ቀዳሚው እንደሆነ የሚታወቅ መሆኑን ያመለከቱት በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያና ማስታወቂያ ዳይሬክተር አቶ ታጠቅ ግርማ፤ ወደ ቻይና ገበያ ቡና በመላክ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። ባለስልጣኑ ከቡና ላኪዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ በሻንጋይ የአስመጪዎች ኤክስፖ የነቃ ተሳትፎ እንድታደረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ''በኤክስፖው ከፍ ያለ ተቀባይነት እንዲኖረን በማድረግ አዎንታዊ ውጤት እናገኛለን'' በማለት አቶ ታጠቅ ተስፋቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በተፈጥሮና በተለያዩ የአረቢካ የቡና ዝርያዎች የምትታወቅ እንደሆነ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ግዛት ወርቁ ለዥንዋ ተናግረዋል። ኤክስፖው በኢትዮጵያ የሚገኙትን የተለያዩ የቡና አይነቶች ለቻይና ገበያ ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርና ለአገሪቱ የቡና ወጪ ንግድ አዲስና አዳጊ ገበያ እንደሚሆን ጠቁመዋል። በቻይና የሚዘጋጀው የአስመጪዎች ኤክስፖ ለኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ከፍተኛ እድል የሚፈጥር መሆኑን በቡና አብቃይነትና ላኪነት የተሰማራው ቀርጫነሴ ቡና የጥራትና የገበያ ዳይሬክተር አስናቀ ካሳ ለዥንዋ ተናግረዋል። “በቻይና ጥሩ ገበያ እንደምናገኝ ተስፋ አለኝ። ኤክስፖው የእኛን አፈጻጸም በማሳደግ ወደ ቻይና የምንልከውን ቡና እንድናሳድግ ያስችለናል” ብለዋል። አገሪቱ ስፔሻሊቲ ቡናዋን ለአለም አቀፉ ገበያ ለማስተዋወቅ የያዘችውን ግብ እውን ለማድረግ ባለፈው ማክሰኞ ከደቡብ ኮሪያ መንግስት ጋር በመሆን የቡና ፓርክ ለመገንባት ስምምነት ላይ ደርሳለች። ፓርኩ በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በሁለቱ መንግስታት ትብብር በአዲስ አበባ በ30 ሄክታር ቦታ ላይ እንደሚገነባም ተገልጿል። “የፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ የአገሪቱን ቡና ለአለም አቀፉ ገበያ ለማስተዋወቅ የማይተካ ሚና ይጫወታል” በማለት የቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክተር ሃይሩ ኑሩ መናገራቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ መዘገቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም