የታዋቂውን የሼህ አሊ የመቃብር ስፍራ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀመረ

75

ጎንደር ኢዜአ ጥቅምት 7 /2012 በ18ኛው ክፍለ ዘመን የሲራራ የንግድ ማእከል የነበረውን የታዋቂውን የሼህ አሊ የመቃብር ስፍራ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ እንዳስታወቀው በ18ኛው ክፍለ ዘመን የሲራራ የንግድ ማእከል የነበረውንና የታዋቂውን የሼህ አሊ የመቃብር ስፍራ የቱሪሰት መዳረሻ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ።

የቱሪስት መዳረሻ ስፍራውን መሰረተ ልማት ለማሟላትና ሙዚየም ለማቋቋም 50 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስፈልግ በጥናት ተለይቷል፡፡

በመምሪያው የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አይቸው ታደሰ ለኢዜአ እንደገለፁት መምሪያው የከተማውን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማስፋት የጎብኚዎችን ቆይታ ለማራዘም አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው።

በ18ኛ ክፍለ ዘመን ሀገሪቱ ከውጪው አለም ጋር ስታካሂድ በነበረው የንግድ ግንኙነት በጎንደር ከተማ አዲስ አለም የተባለው ቦታ የሲራራ ንግድ የሚካሄድበት ታሪካዊ ስፍራ ሆኖ ማገልገሉን አውስተዋል።

በዘመኑ የሲራራ ንግድ ከመላ ሀገሪቱ የሚመጡ ነጋዴዎች ጎንደር ላይ በማረፍ ወደ ሱዳን ፣ ቀይ ባሕርና የመን ድረስ ተሻግረው የንግድ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱበት ታሪካዊ ቦታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበቅሎ፣ በአህያ ፣ በግመልና በዝሆን ጭምር በሚካሄደው የንግድ እንቅስቃሴ ወርቅን የመሳሳሉ የከበሩ ማእድናትን ጨምሮ የዝሆን ጥርስ ፣ እጣንና አሞሌ ጨው ከፍተኛ ስፍራ የሚይዙ የንግድ እንቅስቃሴዎች ነበሩ።

በዚሁ ስፍራ ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጪው አለም ከ200 በሚበልጡ ሀገሮች በእስልምና ሃይማኖታዊ መሪነታቸውና አስተምህሮታቸው ታላቅ ስፍራ የሚሰጣቸው የሼኽ ዓሊ የመቃብር ስፍራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ታላቅ ተሰሚነት ያላቸው የእስልምና መሪው ዓመታዊ በዓል በየአመቱ በሚያዚያ ወር በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርአት ላለፉት 200 ዓመታት በስፍራው ሲከበር ዘመናት መሻገሩን ገልጸዋል፡፡

መምሪያው ስፍራውን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ እንዲቻልም ከጎንደር ዩንቨርሲቲና ከከተማው እስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጋር በመቀናጀት በባለሙያዎች ጥናት ሲያካሂድ ቆይታል።

በመሆኑም አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የመንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ የቱሪስት ማረፊያ ቤቶችና ሙዚየም ለመገንባት እስከ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስፈልግ በፕሮጀክቱ ጥናት ተካቶ ቀርባል።

ፕሮጀክቱን ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን የጠቆሙት ቡድን መሪው በቅርቡ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የምክክር ጉባኤ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

አዲሱ መዳረሻ በተለይ የአረቡ አለም ቱሪስቶችን ወደ አካባቢው ለመሳብ ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአረብ ሀገራት ኤምባሲዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጎንደር ሙስሊም የቱሪዝም እንቅስቃሴ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ ሽኩር መኮንን በበኩላቸው አዲሱን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ለቱሪስቶች ክፍት ለማድረግ ከመምሪያው ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የቱሪስት መዳረሻ ስፍራው የአረብ ሀገራትን ትስስር የሚያጠናክር ነው ያሉት አቶ ሽኩር የከተማውን የቱሪስት ፍሰት በመጨመር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በጎንደር ከተማ በአለም ቅርስነት የተመዘገበውን የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስት ጨምሮ በውጪና በሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የሚጎበኙ ስምንት ያህል ታሪካዊና ጥንታዊ የመስህብ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም