በመንግስት ንብረት አወጋገድና ግዥ ላይ የሚታየውን ብክነት እንዲታረም ተጠየቀ

144

አሶሳ ኢዜአ ጥቅምት 04 / 2012  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመንግስት መሥሪያ ቤቶች በንብረት አወጋገድና ግዥ አፈጻጸም ረገድ የሚታዩ ብክነቶችን እንዲታረሙ አንዳንድ የመንግስት ሠራተኞች ጠየቁ፡፡

ከመንግስት ሠራተኞች መካከል አቶ ሳምሶን ተፈራ እንደሚሉት በክልሉ በተለይም በየወረዳው በሚገኙ መስሪያቤቶች መኪኖችና ሞተር ብስክሌቶች በቀላሉ ተጠግነው ለአገልግሎት መዋል ሲችሉ ለከፋ ብልሽት ይዳረጋሉ፡፡

የተወሰኑት ደግሞ  ውስጣዊ አካላቸውን እየተፈታ መወሰዱን  ነው አስተያየት ሰጪው የሚናገሩት ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተበላሹትን ለጨረታ በማቅረብ የተጀመሩ ጥረቶች ቢኖሩም ውስን እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

በበርካታ መስሪያ ቤቶች የሚፈጸሙ ግዥዎች ጥራቸው ዝቅተኛ ሲሆን ዋጋቸው ግን የተጋነነ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ አቶ ድንቁ ተሻለ ናቸው፡፡

የቁሳቁስ ግዥዎች የሚፈጸሙት ተቋማት ጥያቄ ካቀረቡበት ወቅት በጣም ዘግይቶ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የክልሉ የጋራ ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዳርጋቸው ሞላ  ችግሩን ለመቅረፍ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አገልግሎት ያቆሙትን ተሸከርካሪዎች በጨረታ እዲወገዱ በማድረግ ረገድ የሚበረታታ ውጤት ቢኖርም አሁንም በርካታ ተሸከርካሪዎች በየተቋማቱ ጊቢና በየመጋዘኑ ተቀምጠው እየተበላሹ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች ስራው ከተጠናቀቁ በኋላ በብልሽትና በሌሎችም ምክንያቶች በየቦታው በስብሰው የሚቀሩ ማሽኖች፣ ኮንቴነሮችና ትላልቅ ብረታ ብረቶች መኖራቸውን አክለዋል ተናግረዋል ፡፡

የችግሩ ምንጭ በመንግስት ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠታቸው ነው ያሉት አቶ አንዳርጋቸው አገልግሎቱ የህግ መሠረት አለመኖሩ ተጠያቂ ማድረግ እንዳልተቻለ አስታውቀዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ክልሉ በሚያወጣው አገር አቀፍ ጨረታ የሚሳተፉ ተጫራቾች መጥፋት በመንግስት ግዥ ላይ ጫና መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በክልሉ የሚገኙ 104 ግዥ ፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የተወሰኑ ግዥዎችን በራሳቸው እንዲፈጽሙ መፈቀዱን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የግዥ ዋጋ ግነትና ጥራት ችግር እንዳስከተለ ዳይሬክተሩ ጠቁመው ለአብነትም 17 ሺህ ብር የሚሸጥ ላፕቶፕ ኮሚፕዩተር 23 ሺህ ሲቀርብ ጨረታው እዲታገድ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በርካታ የመንግስት ተቋማት ግዥ በሚፈጽሙበት ወቅት አቅራቢው ዕቃ ሳይቀርብ ክፍያ እንደሚፈጽሙ ጠቁመው ከግዥ በኋላም ቢሆን የንብረቱን የጥራት ደረጃ ሳያረጋግጡ በሚረከቡ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል ።

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ዲቢሳ በክልሉ በመንግስት ተቋማት በንብረት አወጋገድ ብቻ ሳይሆን በሰፋፊ መሬት ላይ የሚገኝ የባህርዛፍ ተክል ለሽያጭ በማቅረብ ረገድም ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል ።

ሃብቱን በማስተዳደር ረገድ ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲኖረው ለማድረግ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ጠቅሰው በቅርቡ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ ሲጸድቅ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም