የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሌሎች አገሮችን ተጽዕኖ ለመቋቋም የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች

112

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 06/2012 የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሌሎች አገሮችን የምጣኔ ኃብትና የፖለቲካ ተጽዕኖ ለመቋቋም በጋራ ለመሥራት የሚያስችል አቋም እንዲኖራቸው ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች።

የቀይ ባህር ደህንነትም ኢትዮጵያ በእጅጉ እንደሚያሳስባትና በባለብዙ ወገን ድርድር የቀይ ባህር ኮሪደር ችግሮቹን ለመፍታት ፍቃደኛ መሆኗን ተናግራለች።

የኢትዮጵያ የውጭና የደህንነት ፖሊሲ ከአካባቢያዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ያነጻጸረ የሁለት ቀን የምክክር መድረክ በአፍሪካ ኅብረት ዛሬ ተጀምሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ እንደተናገሩት፤ የገልፍ አገሮች ከአፍሪካ ቀንድ ጋር ባላቸው ቅርበት የተነሳ የተቆራኙ ናቸው።

ከዛም ባለፈ አካባቢው ከገልፍና ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ታሪካዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ መቀራረቦች እንዳላቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም በአካባቢው የገልፍና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችን የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ተጽዕኖ ለመቀነስ  የጋራ አቋም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

 በተለይም ደግሞ ተመጋጋቢ የጋራ እቅድ በማውጣት ተጽዕኖውን መቋቋም እንደሚገባ አሳስዋል።

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ኮሪደር ሠላምና ደህንነት ጉዳይ እንደሚያሳስባትና ለዚህም ደግሞ የባለ ብዙ ወገን ድርድር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ያም ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢጋድ ጥላ ሥር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ''ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ በሚደረጉ የትኛውንም አይነት መድረኮች ለመሳተፍ ፍቃደኛ ነች'' ብለዋል።

''የዚህ አይነቱ የምክክርና የውይይት መድረክ ደግሞ በቀይ ባህር ላይ ያሉትን ደካማና ጠንካራ ጎን ለመለየት ብቻ ሳይሆን መፍትሄ ለማምጣትም ያስችላል'' ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ተቋማትም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በሚያሂዱት መድረክ ሁሉ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ይህም ደግሞ በቀይ ባህር ዙሪያ ያለውን ችግሮች እንዲሁም መልካም አጋጣሚዎች ለመገምገምና ውሳኔ ለማሳለፍ ምቹ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የማሻሻል ሥራ መጠናቀቁን ገልጸው፤ በመንግሥት ከፍተኛ አካላት ለማጸደቅ በመጠባባቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፖሊሲው ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ጉዳዮችን ከግምት ያስገባና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተልዕኮ የመፈጸም ብቃት እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍንና የጋራ ልማት ለማምጣት የምታደርገውን አዎንታዊ ሚና በኢጋድ ማዕቀፍ ሥር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ቀጣናው በርካታ ስደተኞችን በመጠለያ ጣቢያ እንዲሁም ተፈናቃዮች የሚገኙበትና የተለያዩ ችግሮችን የሚያስተናግድ ቢሆንም ወደ የተሻለ ሰላምና ብልጽግና እያመራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሽብርተኝነት፣ የባህር ደኅንነት አለመኖርና አዳዲስ ቀጣናዊ የፖለቲካ ችግሮች መቀስቀስም ቀጠናውን ውስብስብ ባህሪ እንዲላበስ ያደረገው መሆኑን አብራርተዋል።

አሁንም ግጭቶች በአካባቢው ቢኖሩም የመቆጣጠሩ ሥራ እምርታ እያሳየ ነው፤ ለዚህም ደግሞ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሠላም ሥምምነት አዎንታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በደቡብ ሱዳን ያለው የሰላም ሁኔታ እንዲሻሻል ሁሉን አቀፍ የመፍትሄ ሥራዎች በኢጋድ ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮጵያ ድጋፏን ታጠናክራለች ብለዋል።

በተመሳሳይ በሶማሊያ ጠንካራ የጸጥታ ተቋማት ለመገንባት በአፍሪካ ኅብረት በኩል የሚሰራውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም