የህግ ታራሚዎች የአርሶ አደሩን የሰሊጥ ሰብል በመሰብሰብ ላይ ናቸው

67
ሁመራ ኢዜአ ጥቅምት 06/2012 በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የደረሰ የሰሊጥ ምርት ለብልሽት እንዳይዳረግና እንዳይባክን የህግ ታራሚዎች በአጨዳና በምርት መሰብሰብ ስራ እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑን የአካባቢው አርሶ አደሮች ገለፁ። አርሶ አደሮቹ እንዳሉት በዘንድሮ የመኽር አዝመራ የለማውን የሰሊጥ ሰብል ለመሰብሰብ ከፍተኛ የየጉልበት ሰራተኞች እጥረት አጋጥሞ ነበር ። በዞኑ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሚገኙ የህግ ታራሚዎች አርሶ አደሩን ለመርዳት ያደረጉት ድጋፍ በአካባቢው የጉልበት ሰራተኞች እጥረት ባጋጠመበት ወቅት በመሆኑ ጠቀሜታው የላቀ ነው ብለዋል ። በትግራይ ምእራባዊ ዞን በቃፍታ ሁመራ ወረዳ የሰሊጥ አምራች አርሶ አደር ፀሃየ ገ/መድህን በሰጡት አስተያየት የጉልበት ሰራተኛ እጥረት በማጋጠሙ የደረሰው የሰሊጥ ምርቴን ለብልሽትና ለብክነት ይጋለጣል የሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር ብለዋል ። የህግ ታራሚዎቹ ማሳቸው ድረስ መጥተው በአጨዳና በመሰብሰብ ስራ እገዛ ስላደረጉላቸው የሚጠብቁትን ምርት ሳይጎዳ መሰብሰብ እንደቻሉ ተናግረዋል ። ሌላው ሰሊጥ አምራች አርሶ አደር ተስፋይ ገ/ስላሴ እንደገለጹት ደግሞ የህግ ታራሚዎቹ ድጋፍ የላቀ ዋጋ እንዳለው ገልጸው የእስር ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ወደ ህብረተሰቡ በሰላም እንዲቀላቀሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። ከህግ ታራሚዎች መካከል ወጣት ዮናስ መሰለ በሰጠው አስተያየት ስራውን በራሱ ሙሉ ፈቃድ ለመስራት የተነሳሳው የሰሊጥ ሰብል ጊዜ የማይሰጥና በቀላሉ ማሳ ላይ እያለ ስለሚበላሽ ነው ብሏል። ‘’የአካባቢውን ህዝብ ለህግታራሚዎች ያለውን ቅን ሃሳብና ድጋፍ እኔም በተግባር ምላሽ ለመስጠት በማሰብ በሰሊጥ መሰብሰብ ተግባር ተሳታፊ ሆኛለሁ  ‘’ ያለው ደግሞ ሌላው የህግታራሚ ወጣት ሃፍቶም ፍጹም ነው። የትግራይ ምእራባዊ ዞን ማረሚያ ቤት የልማት ኦፊሰር ኮማንደር ብርሃነ ለገሰ እንደገለፁት በዞኑ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ከ1ሺህ 600 በላይ የህግ ታራሚዎች ለ10 ተከታታይ ቀናት የሰሊጥ ሰብል በመሰብሰብ ስራ መሳተፋቸውን ተናግረዋል። የማረሚያ ቤቱ የህግ ታራሚዎች ከዚህ በፊትም የጉልበት ሰራተኞች እጥረት ባጋጠመበት ወቅት ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ኮማንደሩ አስታውሰዋል ። የማረሚያ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ሓዱሽ ኣባይ በበኩላቸው የህግ ታራሚዎች አርሶ አደሩን ለማገዝ ያሳዩት ፍላጎትና ተግባራዊ ድጋፍ በተጨባጭ የባህሪ ለውጥ ማምጣታቸውን በተግባር የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም